ቀጥታ፡

የክልሉ መንግስት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ትኩረት ሰጥቷል-ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ

ጅግጅጋ ፤ሰኔ 2 /2018 (ኢዜአ)፦ የክልሉ መንግስት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ትኩረት መስጠቱን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ገለጹ፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ፤ በክልሉ ፋፈን ዞን አውበሬ ወረዳ ሼደር ከተማ የተገነባውን አዳሪ ትምህርት ቤት መርቀው በይፋ ስራ አስጀምረዋል።


 

ርዕሰ መስተደድሩ አቶ ሙስጠፌ በወቅቱ፤ በክልሉ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት የተማረ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

አዳሪ ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑም የክልሉ መንግስት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የሼደር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች እና የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግስት ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት ትምህርት ቤቱን በማስገንባት ለአገልግሎት በማብቃቱ ምስጋና አቅርበዋል።


 

ትምህርት ቤቱ የአስተዳደር ቢሮዎችን፣ የመማሪያ ክፍሎችን፣ የተማሪዎችና የመምህራን ማረፍያ ክፍሎችን፣ ቤተ መፃሕፍት እና ሌሎች ለትምህርት አገልግሎት ጠቃሚ የሆኑ ክፍሎችን አካቶ የያዘ መሆኑ ተገልጿል።

 የትምህርት ቤቱ ግንባታ 138 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገበትም በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም