ቀጥታ፡

በአፋር ክልል በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ በተቋቋሙ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች ድምፃቸውን እየሰጡ ነው

ሰመራ፤ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ በተቋቋሙ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች ድምፃቸውን እየሰጡ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኀላፊ ጣሃ ዓሊ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ወይም በልዩ ሁኔታዎች በታቀደው መደበኛ የድምፅ መስጫ ቀን መሳተፍ ላልቻሉ ዜጎች የተራዘመ ወይም ልዩ የድምፅ መስጫ ቀን ያመቻቻል።

ይህ አሠራር ማንኛውም ድምፅ የመስጠት መብት ያለው ዜጋ ከዴሞክራሲያዊ ሂደቱ እንዳይገለልና የምርጫው አካታችነት እንዲረጋገጥ ይረዳል።

ቦርዱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ልዩ የድምፅ መስጫ ቀናትን በማመቻቸት ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ ሲያደርግ ቆይቷል።

በዚህም መሰረት በሀገር ውስጥ በሚገኙ መጠለያዎችና በወታደራዊ ካምፖች ልዩ ጣቢያዎችን በማቋቋም ዜጎች ድምፅ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።


 

በዚህ ጉዳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኀላፊ ጣሃ ዓሊ እንደገለጹት፤ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ዛሬ ድምጽ እየተሰጠ ነው።

መራጭ ዜጎችም ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በክልሉ ባሉ 19 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምጽ እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዱብቲ፣ ገዋኔ፣ አሚባራና ገለአሎ ምርጫ ክልሎች ስር በሚገኙ አስራ ዘጠኝ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎቹ የሚገኙ ዜጎችም ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚፈልጉትን ፓርቲ በመምረጥ ላይ እንደሚገኙ አቶ ጣሃ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም