በመጪው ክረምት ወቅት ሊኖር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው ክረምት ወቅት ሊኖር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 2 /2018 (ኢዜአ)፦በክረምት ወቅት ሊኖር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥ መቀነስ የሚያስችሉ ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ገበየሁ ሊካሳ (ዶ/ር) የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት እና መጪውን የክረምት ወቅት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው እንደገለጹት፤ የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ተጨባጭ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 62 ሺህ 274 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመካከለኛ መስመር ፍተሻ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ የ67 ሺህ 131 ትራንስፎርመሮችን የምርመራ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም ለኃይል መቆራረጥ መንስኤ ከሆኑ የመጀመሪያው ዙር ግኝቶች ውስጥ በዲስትሪቢውሽን ኔትወርክ 92 በመቶ፣ በዲስትሪቢውሽን ትራንስፎርመሮች ደግሞ 86 በመቶ በሚሆነው የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
ከተሠሩ ሥራዎች መካከል በመስመር ውስጥ የገቡ ዛፎችን የማስወገድ ፣ ያዘመሙ አልያም ያረጁ የእንጨት ምሶሶዎችን የመቀየር እንዲሁም ለኤሌክትሪክ መቆራረጥ መንስኤ የሆኑ ኢንሱሌተሮችን የመቀየር ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በራስ የፋይናንስ አቅም 3 ሺህ 99 ኪሎ ሜትር መካከለኛና ዝቅተኛ መስመር ግንባታ መከናወኑን ጠቁመው፣ 1 ሺህ 579 ነባር ዲስትሪቢውሽን ትራንስፎርመሮች ላይ የአቅም ማሻሻያ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
በራስ አቅም እና በዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ የኔትወርክ ማሻሻያ ፕሮጀክቶችም ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የኃይል መቆራረጥን ለመከላከል በተሠሩ ሥራዎች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው በመጪው ክረምት የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም የፕሮጀክት ሥራዎችን እስከ ሰኔ 30 ለማጠናቀቅ ግብ ተይዞ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
አገልግሎቱ ለጥንቃቄ ሲባል የሚደረጉ የዕቅድ ኃይል መቆራረጥ መርሃ ግብሮችን ከአንድ ቀን በፊት በአገልግሎቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እንዲሁም በተለያዩ የዲጂታልና መደበኛ ሚዲያ አማራጮች ለሕዝብ እንደሚያሳውቅም ጠቁመዋል።