የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ላይ አቋማችን የጸና ነው-የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ላይ አቋማችን የጸና ነው-የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበርና ሉዓላዊነቷን የማስጠበቅ ጉዳይ ላይ አቋማችን የጸና ነው ሲሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ታሪክ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የተቃረኑ ባንዳዎች ሁሉ ከስመዋል፤አሁን ያሉትም የሚገጥማቸው ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ ይሆናል ብለዋል።
የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር፣የግዛት አንድነትን መጠበቅ እና የውስጥ ሰላምን ማስፈን እንደ ዋና ብሔራዊ ጥቅም የሚወሰድ መሆኑ ይታወቃል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንኑ ለማስከበር እና ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል።
በአንድ ወቅት የባሕር በር የነበራት ኢትዮጵያ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የባሕር በር እንድታጣ የተደረገበት ሁኔታ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።
በዚህ ረገድ መንግሥት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጥረት እያደረገ ሲሆን ዜጎችም መሠረታዊ አጀንዳቸው አድርገውት ለምላሹ እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ በተቃራኒ አንዳንዶች ከባዕዳን ጋር በመሰለፍ በባንዳነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጻረሩ እንዳሉ የሚታወቅ ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ በኢትዮጵያ ታሪክ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በመቃረን የሚቆሙ ባንዳዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።
እነዚህ አካላት የከሰሙ መሆኑን አንስተው፥ አሁን ያሉትም የሚገጥማቸው ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ እና የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ታሪኩ ድንበሩ፤ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለድርድር የሚቀርብ መሆን የለበትም ብለዋል።
በመሆኑም ሁላችንም የሀገር ሰላምን በጋራ የመጠበቅ፣ የኢኮኖሚ ልማት ሥራዎችን በጋራ ማስቀጠል እና ከውጭ የሚቃጡ ጥቃቶችን በጋራ የመመከት ግዴታ አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበርና ሉዓላዊነቷን የማስጠበቅ ጉዳይ ላይ የሁላችንም አቋማችን የጸና ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ኡመር አብዱራህማን፤ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሚፎካከረው ከምንም በላይ ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም ለመሥራት መሆን አለበት ብለዋል።
ከዚህ በተቃራኒ በመቆም በሀገር ብሔራዊ ጥቅምና በዜጎች ደኅንነት ላይ መሥራት የባንዳነት ተግባር ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የሕዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሱራፌል እሸቱ፤ የትኛውም የፖለቲካ ተዋናይ ይሁን ዜጋ በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ የተለየ አቋም መያዝ ተገቢነት የሌለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመሆኑም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ጨምሮ ሌሎችም ኢትዮጵያን በሚመለከቱ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ አቋማችን የጸና እና የማይናወጥ ነው ብለዋል።