የሀገራችንን ዳር ድንበር ከማስከበር ጎን ለጎን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በመጠቀም ድምፃችንን ሰጥተናል-የሰሜን ምስራቅ ዕዝ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራችንን ዳር ድንበር ከማስከበር ጎን ለጎን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በመጠቀም ድምፃችንን ሰጥተናል-የሰሜን ምስራቅ ዕዝ አባላት
ሰመራ፣ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ) የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ከማስከበር ጎን ለጎን፣ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በመጠቀም ድምፃችንን ሰጥተናል ሲሉ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምስራቅ ዕዝ አባላት ገለፁ።
በኢፌዴሪ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ መሠረት፣ ማንኛውም መራጭ ድምፅ ለመስጠት በሚኖርበት ወይም በቋሚነት በሚሠራበት አካባቢ ተመዝግቦ መምረጥ እንዳለበት ይደነግጋል።
ሆኖም ግን፣በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎች እና የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር በተለያዩ ግንባሮችና ካምፖች ውስጥ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በመደበኛው የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ለመስጠት የሚቸገሩበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ይህን መሠረታዊ መብት ለማስከበርና የምርጫውን አካታችነት ለማረጋገጥ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ልዩ መመሪያዎችን በማውጣት ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን ያደራጃል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም በልዩ ሁኔታ ላይ ባሉ በሀገር ውስጥ መጠለያ ሊሚገኙና በመከላከያ ካምፖች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ዛሬ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የሰሜን ምስራቅ ዕዙ አባላት እንዳሉት፥ ሰራዊቱ በታላቅ ጀግንነት የሀገሩን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር በማስከበር ላይ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎን ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ለሀገር ይበጃል ላሉት ፓርቲ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የሰሜን ምሰራቅ ዕዝ ኦዲት ኀላፊ ተወካይ ሻለቃ ንጋቱ ኩምሳ፤ ሰራዊቱ በላቀ ጀግንነት የሀገሩን ዳር ድንበር ከማስከበር ጎን ለጎን በዛሬው ዕለት በመምረጡ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
በቀጣይነትም በምርጫው ካሸናፊው ፓርቲ ጎን በመሆን የኢትዮጵያን ሰላም የማረጋገጥ፣ ዳር ድንበርን በቆራጥነት የማስከበር ሚናችንን እንወጣለን ብለዋል።
ሻለቃ ባሻ አባተ አርሲኖ በበኩላቸው፤ የተሰጠንን ሀገራዊ ግዳጅ ለመወጣትና የሀገራችንን ዳር ድንበር ለማስከበር የምንጊዜም ዝግጁነታቸውን ገልፀው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን በምርጫው መሳተፍ በመቻላቸው እንዳስደሰታቸው ነው ያስረዱት።
በምርጫው በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ ይህም ለሶስተኛ ጊዜያቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
መቶ ዓለቃ ኢያሱ ጩማ፤ የሀገሬን ዳር ድንበር እያስከበርኩ በዚህ ወቅት ዴሞክራሲያዊ መብቴን ተጠቅሜ መምረጥ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በነፃነት መምረጥ መቻላቸውን የተናገሩት ደግሞ አስር ዓለቃ ታመነ ተሻለ ናቸው።
የሀገሬን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር እየጠበቅኩና ሰላሟን እያስቀጠልኩ ከዚህ ጎን ለጎን መምረጥ በመቻሌ ደስ ብሎኛል ብለዋል።