ቴክኖሎጂን ከሀገራዊ ርዕያችን ጋር ማጣመራችን ለሀገር የሚገባውን ፈጣን እድገት እውን ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ መሆናችንን ያሳያል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ቴክኖሎጂን ከሀገራዊ ርዕያችን ጋር ማጣመራችን ለሀገር የሚገባውን ፈጣን እድገት እውን ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ መሆናችንን ያሳያል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሰኔ 2 /2018 (ኢዜአ)፦ቴክኖሎጂን ከሀገራዊ ርዕያችን ጋር ማጣመራችን ለሀገር የሚገባውን ፈጣን እድገት እውን ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ መሆናችንን ያሳያል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነቡ ቤቶች የሚገኙበት የግንባታ ሳይት ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
በዚህ ሳይት ሦስት የላቁ የግንባታ ዘዴዎች በጥምረት ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን፣ እነሱም የ3ዲ ህትመት (3D printing)፣ የቅድመ-ዝግጅት ቀላል የአረብ ብረት ግንባታ እና የኮንቴይነር መኖሪያ ቤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
እያንዳንዳቸው ግንባታዎች ትክክለኛውን ቴክኖሎጂ ስንጠቀም ፍጥነት እና ጥራት እርስ በእርስ የማይጋጩ መሆናቸውን ያረጋገጡ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ጥራታቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶችን ከወራትና ከዓመታት ይልቅ በጥቂት ቀናት እና ሳምንታት ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል የታየበት ህያው ምስክር መሆኑንም አስታውቀዋል።
ይህ አይነቱ የላቀ ፈጠራ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በቀላሉ ሊተገበር፣ ሊደገም እና ሊስፋፋ የሚችል መሆኑንም ያብራሩት።
ይህም የሀገራችንን የቤት ልማት ፕሮግራም አቅጣጫ በከፍተኛ ደረጃ የመቀየር ኃይል አለው ብለዋል።
ቴክኖሎጂን ከሀገራዊ ርዕያችን ጋር ማጣመራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ መሰል በተግባር የተገለጡ ስራዎቻችን ደግሞ ለሀገር የሚገባውን ፈጣን እድገት እውን ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ በቁርጠኝነት እየተጓዝን መሆናችንን በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።