ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አርሶ አደሮች በምርት መሰብሰቢያ ወቅት የሚገጥማቸውን የገንዘብ ዕጥረት እየቀረፈ ነው

አዲስ አበባ፤ሰኔ 2/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግብርና ኢኮኖሚን በማሳለጥ አርሶ አደሮች በምርት መሰብሰቢያ ወቅት የሚገጥማቸውን የገንዘብ ዕጥረት እንዲቀረፍ እያደረገ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ታዜር ገብረእግዚአብሔር ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዕቃ ማከማቻ /መጋዘን/ ደረሰኝ ሥርዓት ደንብ ቁጥር 589/2018 ዓ.ም ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት አርሶ አደሮች፣ ማህበራትና የግብርና ምርት አቀናባሪዎች ደረጃውን የጠበቀ ምርት በመጋዘን በማስቀመጥ በደረሰኝ አማካኝነት የባንክ ብድር የሚያገኙበት አሰራር ነው።

ይህ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት አርሶ አደሮች በምርት መሰብሰቢያ ወቅት የሚገጥማቸውን የገንዘብ ዕጥረት ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካኝነት ተግባራዊ መሆን ችሏል።

ቀደም ሲል አርሶ አደሮች በገንዘብ እጥረት ምክንያት ምርታቸውን በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዱ የነበረ ሲሆን፣ ይህም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በምርታማነትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

አዲሱ አሰራርም አርሶ አደሮች ምርታቸውን በደረሰኝ በማስያዝ ብድር እንዲያገኙና ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ታዜር ገብረእግዚአብሔር በመድረኩ እንዳሉት፤ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት የገጠርና የግብርና ልማት ሽግግርን በማፋጠን የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

የአሰራር ሥርዓቱም አርሶ አደሮች፣ ህብረት ሥራ ማህበራትና የግብርና ምርት አቀናባሪዎች በመጋዘን ደረሰኝ አማካኝነት አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ከ20 ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም ግልፅ ተቆጣጣሪ ባለመኖሩ ገቢራዊ ሳይደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በሕግና መመሪያ ተቆጣጣሪና ባለቤት በማበጀት ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።

አርሶ አደሮች ምርታቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ በማከማቸት ብድር ማግኘት፣ መቼና እንዴት መሸጥ እንዳለባቸው የማሰቢያ ጊዜ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

ሥርዓቱንም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እንዲሆን በማስቻል የፋይናንስ ተቋማትን የሚያበረታታ ደንብ፣ መምሪያና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (የአግራ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ይኼነው ዘውዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የደረሰኝ ሥርዓቱ የአርሶ አደሮችን ድካም የሚመጥን የተሻለ ገበያና ዋጋ ማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአርሶ አደሮችን ምርታማነት በማሻሻልም የገበያ አቅርቦትን ጨምሮ በተመዘገበ መጋዝን በሚያስቀምጡት ምርት በደረሰኙ የብድር ዋስትና የሚያገኙበትን እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የአርሶ አደሮችን የመደራደር አቅም እንደሚያሳድግ ገልጸው፤ የብድር መስፈርቶች የአርሶ አደሮችና ማህበራትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል።

የደረሰኝ ሥርዓቱ በኢትዮጵያ አበረታች ጅምር መሆኑን በማንሳት፤ የአርሶ አደሩን ህይወት በአስተማማኝ ሁኔታ በመቀየር የግብርና ሽግግር እንደሚያሳካ ተናግረዋል።

አግራ ግብርናን ለማዘመን ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር በ15 የአፍሪካ ሀገራት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ የዕዳ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ውጤታማነት በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም