ቀጥታ፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 56ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 56ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

56ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብስባ ውሳኔዎች፦

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የመካከለኛ ዘመን (2019-2023) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ ነው፡፡ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካሉበት ተግዳሮቶች እየተላቀቀና የኢኮኖሚው መሰረቶችም እየተጠናከሩ መጥተዋል፡፡ ማዕቀፉ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲያስችልና በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊስካል ታሳቢዎች ላይ በመመስረት የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት ዝግጅት መነሻ ሆኖ እንዲያገለግል ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በማዕቀፉ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡


 

2. በመጨረሻም ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የ2019 የፌዴራል መንግስት በጀት የአስር አመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነው የ2019-2021 የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችንና የመካከለኛ ዘመን (2019-2023) የማክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ማዕቀፍን መሰረት በማድረግ፣ የ2018 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ፣ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና አላማዎች እንዲሁም በመንግስት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የመንግስትን የፋይናንስ አቅም እና አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮና ሃላፊነት አንጻር የሚያስፈልገውን ወጪ በመገምገም ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

በዚሁ መሰረትም ለመደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልል መንግስታት ድጋፍ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የሚውል 2,339,268,126,738 (ሁለት ትሪሊዮን፣ ሶስት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ቢሊዮን፣ ሁለት መቶ ስድሳ ስምንት ሚሊዮን፣ አንድ መቶ ሀያ ስድስት ሺ፣ ሰባት መቶ ሰላሳ ስምንት ብር) በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡


 

ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግስት የ2019 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም