ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ታሪካዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) በመካከላቸው ያለውን ለረጅም ጊዜ የቆየ አጋርነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ለምለም ፍስሃ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ዛሬ አቅርበዋል።


 

በዚሁ ወቅትም አምባሳደሯ እና ዋና ጸሐፊው በሁለትዮሽ እና በጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው፣ በኢትዮጵያ እና በኮሚሽኑ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነትና አጋርነት አንስተዋል።

ይህንን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው አዳዲስ የትብብር መስኮች ዙሪያ የሀሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደር ለምለም ፍስሃ ባለፈው ሳምንት ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የሹመት ደብዳቤያቸውን ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም