ቀጥታ፡

የአፍሪካ እና አውሮፓ የጤና እና ሰብአዊ ፈተናዎች ምላሽ አጋርነት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ጋር ያለውን የጤና እና ሰብአዊ ፈተናዎችን የመከላከል አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኝነቱን ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የአውሮፓ ህብረት የእኩልነት፣ ዝግጁነት እና የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ሃጃ ላህቢብን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለዓለም አቀፍ የጤና ፈተናዎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ ያነሱት ሚኒስትሩ፣ በተለይም የኢቦላ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው የጋራ እንቅስቃሴ ህብረቱ ላሳየው አጋርነት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።


 

ህብረቱ የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (Africa CDC) ያደረገው ድጋፍ፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ወቅታዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ለኮሚሽነሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነር ሃጃ ላህቢብ በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የጋራ መፍትሄ የሚሹ የጤና እና የሰብአዊ ፈተናዎችን በትብብር ለመፍታት ህብረቱ ዝግጁ እንደሆነ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም