አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዕውቀትን ለትውልድ የሚያሻግር ምኅዳር እየገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዕውቀትን ለትውልድ የሚያሻግር ምኅዳር እየገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዕውቀትን ለትውልድ የሚያሻግር ምኅዳር እየገነባ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ40 በላይ የመጽሐፍት አከፋፋዮች፣ አሳታሚዎችና የመጽሕፍት መደብሮች የሚሳተፉበትን 18ኛውን ዓመታዊ የመጽሐፍት ዓውደ ርዕይ በስድስት ኪሎ ግቢ ይፋ አድርጓል።
ከሰኔ 1 ቀን እስከ ሰኔ 7/2018 ዓ.ም የሚቆየው ዓውደ ርዕይም በሁሉም የዕውቀት ዘርፎች የሚያተኩሩ ነባርና አዳዲስ መጽሐፍት ለአንባቢያን በቅናሽ ዋጋ ቀርበዋል፤ አዳዲስ መጽሐፍትም ይመረቃሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ ከ50 ዓመታት በላይ በርካታ መጽሐፍትን ሲያሳትምና ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት ጉዞም የፕሬስ አቅምን በማጎልበና የዘመን ገበያን በመጠቀም የመጽሐፍትን ተደራሽነት የሚያሰፉ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዕውቀትን ለትውልድ የማሻገርና ተቋሙ ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ደርብ አዶ (ዶ/ር)፤ ዓውደ ርዕዩ የመጽሐፍት ሽያጭ፣ የደራሲያን የልምድ ልውውጥ፣ ውይይትና የፕሬስ ሕትመቶች ምርቃት ይካሄድበታል ብለዋል።
በቀጣይም የዩኒቨርሲቲውን ፕሬስ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት የሚያሰፉ ተግባራትን የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዓውደ ርዕዩ ከተሳተፉት መካከል የክብሩ መጽሐፍት መደብር ተወካይ ሜሮን ይልማ፤ ዓውደ ርዕዩ የንባብ ባህል እንዲሁም የተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ሕፃናት በጨዋታ መልክ የሚያስተምሩ መጫወቻዎችን ይዘው የቀረቡት የፊት በር ቶይስ ተወካይ ሚካኤል ግርማ በበኩላቸው፤ ዓውደ ርዕዩ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቻይንኛ ቋንቋ መምህር ሶንግ ሩዶንግና ዩሊያን ዡ ዩሉ በበኩላቸው፤ ዓውደ ርዕዩ ተማሪዎች መጽሐፍት እንዲያገኙና የንባብ ባህል እንዲያዳብሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ዓውደ ርዕዩው በርከት ያሉ መጽሐፍት የቀረቡበት በመሆኑ አንባቢያን የሚፈልጉትን እንዲያገኙ ያስችላል ያሉት ደግሞ መህዲ አብዱረዛቅና ጅሎ ከሚ ናቸው።
በዓውደ ርዕዩ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ (ዶ/ር)፤ ዓውደ ርዕዩ የንባብ ባህልን በማዳበር ወጣቶችና ታዳጊዎች ዕውቀት ማሳደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በቀጣይም ዜጎች የንባብ ባህላቸውን በማጎልበት በዕውቀትና ምክንያታዊነት የተመሰረተ ዕሳቤን ማበልፀግ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።