ቀጥታ፡

የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ የሕዝብን ሀብት ለልማት በማዋል በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ህዝባችን ለአገልግሎት ፍለጋ ጊዜና ገንዘቡን ሳያባክን ሃብቱን ለልማት እንዲያውል የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፤ ለህዝብ የገባነውን ቃል በተግባር መፈፀም መለያችን ነው ብለዋል።

9ኛው አዲስ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት በየካ ክፍለ ከተማ ዛሬ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ፈጣን፣ ግልፅ እና ተደራሽ ለማድረግ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ስራ በ2018 ዓ.ም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስራ ለማስጀመር ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

ለህዝቡ ቃል በተገባው መሰረትም የዛሬውን ጨምሮ ዘጠኝ ማዕከላትን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል።

ይህ አሰራር የአገልግሎት እንግልትን፣ ጉቦ የመጠየቅ ችግርን ለመቅረፍ፣ ተጠያቂነትን እና የህዝብን በክብር የመገልገል መብት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ህዝቡ ለአገልግሎት ፍለጋ ጊዜውንና ገንዘቡን ሳያባክን ሃብቱን ለልማት እንዲያውል ለማድረግ የታቀደውን ግብ በማሳካት የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ ባለ 7 ወለል ህንፃ አዲስ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ላደረጉት አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም