ቀጥታ፡

በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማላቅ የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማላቅ የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድጉ ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በየካ ክፍለ ከተማ የተገነባውን 9ኛ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።


 

ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት፤ የማዕከሉ መገንባት ህብረተሰቡ ፈጣን፣ ግልጽ እና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ቀደም ሲል ከህዝብ ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት የህዝብ እንግልትና ምሬት ምንጭ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻሉን አውስተዋል።

ለህዝብ ጥያቄ ቅድሚያ መስጠት ዋና መገለጫ የሆነው ከተማ አስተዳደሩ፤ ጥራት ላለው የመንግሥት አገልግሎት እንቅፋት የሆኑ ምክንያቶችን ነቀሶ በማውጣት እልባት እየሰጠ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም አልፎ አልፎ ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የዛሬውን ጨምሮ ዘጠኝ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማደራጀት ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ማዕከላት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙላቸው እና የበቃ የሰው ሀይል የተሟሉላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የማዕከላቱ ወደ ስራ መግባት ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበትን አሰራርን እውን በማድረግ በህብረተሰቡ ዘንድ ይነሱ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መቅረፍ ማስቻላቸውን ነው የተናገሩት።

በቀጣይም በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማላቅ የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድጉ ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ዜጎችን ከእንግልትና ከአላስፈላጊ የገንዘብ ወጭ ታድጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም