ቀጥታ፡

በሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ፣ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ከዛምቢያ አቻው ጋር ለሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበዋል።

ከተመረጡት ተጫዋቾች መካከል ግብ ጠባቂዎቹ መቲ ረታ (ልደታ ክፍለ ከተማ) ፣ ኑዳ ሁሴን (አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ) እና ባንቺጊዜ አንተነህ (ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ) ጥሪ ደርሷቸዋል።

ማንጠግቦሽ አድማሱ (አርባምንጭ ከተማ )፣ እየሩሳሌም ኤርሚያስ (መቀሌ 70 እንደርታ)፣ ኤልሻዳይ ዮሴፍ ( ጉለሌ ክፍለ ከተማ) ፣ ቤተልሄም ጌታቸው (ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ)፣ መድኃኒት አለሙ (አርባምንጭ ከተማ)፣ መክሊት መሰለ (ጉለሌ ክፍለ ከተማ) እና ዝናሽ ሰለሞን (ድሬዳዋ ከተማ) በተከላካይ መስመር የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።

በአማካይ ክፍል ናጆክ ዱክ ( የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ)፣ ሊያም ዳንኤል (የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ)፣ ጌጤነሽ ተስፋዬ (ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ)፣ ቢታኒያ አስተረፍ (ሲዳማ ቡና) ፣ ናግዋ ማን (ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ)፣ ኮከብ ደጀኔ (ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ)፣ ኤልሳ መኮንን (ድሬዳዋ ከተማ) እና ሊዲያ ሰለሞን (ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ) በጥሪው ተካትተዋል።

ምህረት ወሰኑ (ሸገር ከተማ)፣ ምህረት አየለ (ቦሌ ክፍለ ከተማ) ፣ ሊዲያ ኢያሱ (ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ) ፣ ሳውያ መሐመድ (ፋሲል ከነማ)፣ እመቤት ዘካሪያስ (ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ)፣ ኦጁሉ ኦዶንግ (ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ) እና ሲርያ ተሾመ (ጉለሌ ክፍለ ከተማ) በአጥቂ መስመር ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም በካፍ የልህቀት ማዕከል በመሰባሰብ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዛምቢያ ጋር የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን ሰኔ 27 እና ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ያደርጋል።

10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች።

ከሞሮኮ ውጪ በማጣሪያ የሚያልፉ አራት የአፍሪካ ሀገራት በመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች ይለያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም