በዞኑ የሰፈነው ሰላም የልማት ሥራዎችን በሙሉ አቅም ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል -ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የሰፈነው ሰላም የልማት ሥራዎችን በሙሉ አቅም ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል -ነዋሪዎች
አምቦ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የሰፈነው ሰላም የልማት ሥራዎችን በሙሉ አቅም ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ምዕራብ ሸዋ ዞን በተለያየ መልኩ ለጸጥታ ችግር ተጋልጠው ከቆዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
የአካባቢውን ሰላም አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት በአካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላም መስፈኑ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸውን በተሻለ ለማከናወን ችለዋል፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ግርማ ሲያ፤ ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው አጋጥሞ የነበረው የጸጥታ ችግር መፈታቱ በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ከዚህም ባለፈ ለብዙ ዓመታት ሲያነሷቸው የነበሩ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ሀይልና የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ለመሆን መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
አሁን የአካባቢያችን ሰላም አስተማማኝ በመሆኑ የልማት ጥያቄዎች እየተመለሱልን ነው፤ እኛም አካባቢያችንን ተደራጅተን እየጠበቅን ነው ብለዋል።
ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ መብራት አስማማው በበኩላቸው፤ በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም እየጠበቅን የዕለት ተዕለት የልማት ስራዎቻችንን ያለምንም ስጋት እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል።
በቀጣይ ሰላምን ዘላቂ ከማድረግ አንጻር ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል፡፡
በአካባቢያችን አሁን ያለው ሰላም አስተማማኝ በመሆኑ በልማት ስራዎች ላይ የምናድረገው ተሳትፎ አድጓል ብለዋል።
በዞኑ የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አለሙ ሂርኮ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ህዝቡ ከመንግስት የጸጥታ መዋቅር ጋር ተባብሮ በአንድነት በመስራቱ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ተችሏል፡፡
በዚህም በወረዳው በሁሉም የገጠርና የከተማ አካባቢዎች ነዋሪዎች መደበኛ የልማት ሥራዎችን ያለምንም የጸጥታ ስጋት እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የወረዳው ነዋሪ ያለምንም የሰላም ስጋት ወጥቶ የዕለት ተዕለት መደበኛ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ የህብረተሰቡን ጥያቄ የሚመልሱ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታም እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዞኑ ሰላምን ለማስፈን በተሰሩ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት ዘላቂ ሰላም መስፈኑን የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳደሪ አቶ አበበ ጨመዳ ናቸው።
በዞኑ ባለፉት አምስት ዓመታት በአንዳንድ ወረዳዎች ላይ የሰላም እጦት አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰው፤ ህብረተሰቡ በየደረጃው ካለ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራቱ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።
በዚህም ቀደም ሲል ተስተጓጉለው የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እየሆኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡