ቀጥታ፡

ፌደራል ፖሊስ የኢትዮጵያን ታሪክና ልዕልና በሚመጥን መልኩ እየሰራ ነው - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ፌደራል ፖሊስ የኢትዮጵያን ታሪክና ልዕልና በሚመጥን እንዲሁም ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተግባራዊ ስራዎች እየሰራ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡

ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ እንደገለጹት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሪፎርም ትግበራ ያካሄደው ተቋሙ አሁን ላይ ወንጀልን አስቀድሞ የመከላከል ጠንካራ ቁመናን ገንብቷል፡፡

ይህም ከተለዋዋጭ ሁኔታ እና ዲጂታሉ ዓለም ጋር እኩል እንዲጓዝ አድርጎታል ብለዋል፡፡


 

ፌደራል ፖሊስ የኢትዮጵያን ታሪክና ልዕልና በሚመጥን መልኩ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በዓለም አቀፍና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል ላይ ስኬታማ ስራ መስራቱን አንስተዋል።

ተቋሙ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በተለያዩ አቅጣጫዎች መረባቸውን በመዘርጋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን ከነመሪያቸው በመያዝ የፍርድ ሂደታቸውን እንዲከታተሉ ማድረጉንም አመልክተዋል።

መሰል የወንጀል ድርጊት የሚከሰትበትን ቀጣና በመለየት ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፤ የብዙ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ በሚገኘው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ በቁርጠኝነት የከወነው ስራ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት አድናቆት የተቸረው ሆኗል ብለዋል።


 

በዚህም ተቋሙ ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ቁጥጥር ላይ አይተኬ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

በዘርፉ ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የተቋሙን ተጽዕኖ ከፍ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።

የወንጀል ድርጊቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየረቀቁ በቴክኖሎጂም እየላቁ ቢመጡም ፌደራል ፖሊስ በዛው ልክ አቅሙን በማጠናከር ዘመኑን በዋጀ መንገድ ተግባሩን መቀጠሉን ማረጋገጣቸውን የዘገበው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም