ቀጥታ፡

በጅማ ዞን የተጀመረው የሻይ ቅጠል ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው

ጅማ፣ ሰኔ 1/2018  (ኢዜአ)፦ በጅማ ዞን የተጀመረው የሻይ ቅጠል ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያሳድግ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር ተናገሩ።

በዞኑ ሸቤ ሶምቦ ወረዳ አርሶ አደሩን ባሳተፈ መልኩ የሻይ ቅጠል ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር እንደገለጹት፤ ዞኑ ለሻይ ቅጠል ልማት ምቹ በመሆኑ አርሶ አደሩን በክላስተር በማደራጀትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ይገኛል።

በዞኑ ከ 60 ሚሊዮን በላይ የሻይ ቅጠል ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ 20 ሚሊዮን የሚበልጠውን የመትከል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።


 

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በ 1 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ቅጠል ማልማት መቻሉን ጠቅሰው፤ የሻይ ቅጠል ልማቱን ይበልጥ አስፋፍቶ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የሻይ ቅጠል ፋብሪካ የማቋቋም ሥራ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛልም ነው ያሉት።

የሸቤ ሶምቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድሳኒ አባ ኦሊ በበኩላቸው፤ በወረዳው በአሁኑ ወቅት በ 500 ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ቅጠል እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በኩታ ገጠም ተደራጅተው ወደ ሥራው ለገቡ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፈጠሩንና ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን አክለዋል።


 

የወረዳው አርሶ አደሮች የሆኑት አባ ዝናብ አባዋይ እና አህመድ ሼከማል በኩታ ገጠም ተደራጅተው በሻይ ቅጠል ልማት ላይ መሰማራታቸውን ገልጸው፤ ከባለሙያዎች የሚደረግላቸው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑንና ወደ ሥራው በመግባታቸው ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው ወጣት አርሶ አደር ሚፍታህ መሐመድ በበኩሉ፤ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተደራጅቶ የሻይ ቅጠል እያለማ መሆኑን ጠቅሶ ወደ ፊት ተጠቃሚ እንደምሆን ትልቅ ተስፋ አለኝ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም