ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን በማጠናከር ፍትሃዊ አገልግሎት ተደራሽ ይደረጋል

ሰመራ፤ ሰኔ 1/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን በማጠናከር ፍትሃዊ አገልግሎት ተደራሽ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ገለፀ።

አገልግሎቱ ከአፋር ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን ለማጠናከር በወረዳዎች የተበታተነውን የፋይናንስ አቅም ወደ ክልል ለማምጣት ያለመ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።


 

በመድረኩ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልገሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ ባለፉት ዓመታት ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የህብረተሰብ ቁጥር የማሳደግ ስራ ተሰርቷል።

በመረዳዳት ላይ የተመሰረተው ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ለማሳካትም የገንዘብ አቅምን ማሳደግ ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልፀዋል።

ለዚህም በክልሉ በ40 ወረዳዎች የሚገኘውን ገንዘብ ወደ አንድ ቋት ለማምጣት መሰራቱ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ለማሳካት የሚስተዋሉ እጥረቶችን በማረም እንደ ሀገር በያዝነው ዓመት ለ70 ሚሊየን ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የጤናውን ዘርፍ በአግባቡ በመምራት የአገልግሎቱን ተደራሽነትና ጥራት ለማስጠበቅ የሃብት አስተዳደር ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ያሲን ሃቢብ ናቸው።

በክልሉ አንድ የሂሳብ ቋት በማዘጋጀት ጠንካራ የጤና መድህን ስርዓት እየተገነባ መምጣቱን ገልጸው ስራውንም በተደራጀ መንገድ ለመምራት ስልጠናዎች በየጊዜው መሰጠታቸውን አስረድተዋል።

ይህም የክልሉን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነት ቁጥር ማሳደግ መስቻሉን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአፋር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ኢድሪስ መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው አገልግሎቱ በ2012ዓ.ም በክልሉ በአይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች መጀመሩን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በ40 ወረዳዎች ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም 158ሺህ አባወራዎችና እማወራዎችን ተጠቃሚ በማድረግ በክልሉ 80 በመቶውን መሸፈን መቻሉን አስረድተዋል።


 

የህብረተሰቡን ጥያቄ በተሟላ ደረጃ ለመመለስና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የክልላዊ ቋት ወደ ትግበራ ለማስገባት ለባለድርሻዎች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በስልጠናው የክልሉ ገንዘብ ቢሮ፣ ሲቪል ሰርቪሰና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ እንዲሁም ከክልሉ ጤና ቢሮ የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ሲሆን ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም