ቀጥታ፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ወረቀት አልባ የሚያደርግ ወሳኝ አቅም እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018(ኢዜአ)፦ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ወረቀት አልባ የሚያደርግ ወሳኝ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ፡፡

ዶክተር ደረጄ  ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ በጤናው ዘርፍ ፈጣንና ቀልጣፋ የአገልግሎት ምኅዳር በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂም የጤና ተቋማትን አገልግሎት በማዘመን ወሳኝ መሰረት መጣሉን አስታውሰዋል።

ለአብነትም የጤና ተቋማትን አገልግሎቶች በኦላይን የዲጂታል ሥርዓት በማሰናሰል ተገልጋዮች ቀልጣፋና ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የኢንተርኔት አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢ የሚገኙ ጤና ተቋማት ጭምር ''በሄልዝ ኔት'' ለማስተሳሰር መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የዲጂታል ጤና አገልግሎቱም የበሽታ መከላከልና አክሞ ማዳን አቅሞችን በማጎልበት ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዲጂታል ጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማስፋት በተከናወኑ ተግባራትም 40 ሶፍትዌሮችን በማልማት ተገልጋዮች የጤና መረጃና አገልግሎት እንዲያገኙና መረጃን በስፋት እንዲሰንዱ እየተደረገ መሆኑን አንሰተዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ወረቀት አልባ የሚያደርግ ወሳኝ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቀጣይም በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት የጤና ምኅዳሩን በዲጂታላይዜሽን የአሰራር ሥርዓት በማሳለጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም