በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የኮሪደር ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የኮሪደር ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል
ባህር ዳር፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የኮሪደር ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
ዓለም አካባቢ ቀን "የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖን መታደግ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
የባለስልጣኑ ዋና ኃላፊ አቶ ተስፋሁን አለምነህ በመድረኩ እንደገለጹት፣ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እያገዘ ነው።
የኮሪደር ልማትም ከተሞችን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ በማድረግ የአካባቢ ጥበቃንና እንክብካቤ ሥራ እንዲፋጠን አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ማንኛውም የልማት ፕሮጀክት ዘላቂነቱ የሚረጋገጠው ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተጣጣመ መልኩ ሲተገበር መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በክልሉ ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመዋል።
በክልሉ የልማት ሥራዎች ከአየር ንብረት ጋር ተጣጥመው እንዲከናወኑ መደረጉ እንደ ጎርፍ እና በረሀማነት ያሉ ችግሮችን ለመቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
በአማራጭ የሃይል አቅርቦት ላይ የተመሰረተ ልማትም የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል።
የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለህብረተሰቡ በዘመናዊ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ትምህርት በመስጠት ለውጥ እየታየ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ይህም ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በባለስልጣኑ የአየር ንብረት ለውጥ አካቶ ትግበራ ዳይሬክተር አቶ አወቀ ይታይ የመወያያ ጽሁፍ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በግብርና፣ በትራንስፖርትና በከተማ ልማት ዘርፎች የአየር ንብረት ጉዳይን አካቶ እየተሰራ ነው።
በማሳያነትም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና በኮሪደር ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።