ቀጥታ፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ ምርምሮችን ችግር ፈቺ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የትምህርት ሚኒስቴር

ሮቤ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ፣ ውጤታማና ወጥ አሠራር እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ለሀገራዊ የልማት ዕቅድ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለተመራማሪዎችና ለመምህራን በዘመናዊ የምርምር ማሻሻያ ስትራቴጂዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።


 

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራ አስፈጻሚ ሰራዊት ሐንድሶ (ዶ/ር) በሥልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ።

"የሀገራት ዕድገት ዋና ምስጢር ጥራት ያለው የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ውጤት ነው" ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ከአካባቢያቸው ባለፈ ለሀገሪቱ የልማት ግብ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው ብለዋል።

ሥልጠናውም ምሁራን በየጊዜው ከሚለዋወጡ ዓለም አቀፋዊ የምርምር ስልቶች ጋር እንዲራመዱ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ ጥራት ያለው ሥልጠና ከመስጠት ጎን ለጎን የተጀመረውን ሀገራዊ ልማት ለመደገፍ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ በትኩረት እየሠራባቸው ከሚገኙ ዋና ዋና የምርምር ዘርፎች መካከል ግብርና፣ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ጤና እና ቱሪዝም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ቀደም ሲል በተናጠል ይሰሩ የነበሩ የምርምር ሥራዎችን በማቀናጀት፣ የተሻለ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ግዙፍ የምርምርና የፕሮጀክት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና ሥልጠናውም ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር)፤ ይህ ዓይነቱ ሥልጠና በጀትን በቁጠባ በመጠቀም ተወዳዳሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ የምርምር ውጤቶችን ለማፍራት የሰው ኃይል አቅምን እንደሚገነባ ገልጸዋል።


 

ሥልጠናው በተለይም በመሠረታዊ የምርምር ሥርዓትና በምርምር ሥነ-ምግባር፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም፣ በምርምር ፈንድ አፈላለግ ስልቶች ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም