የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የኑሮ ጫናን በመቀነስና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ እፎይታ እየሰጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የኑሮ ጫናን በመቀነስና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ እፎይታ እየሰጡ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የኑሮ ጫናን በመቀነስና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ እፎይታ እየሰጡ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።
መንግሥት በቅዳሜና እሁድ ገበያዎችና ተግባራዊ ባደረጋቸው የተለያዩ ኢኒሼቲቮች የምርት አቅርቦትን በማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ ገበያን በማረጋጋት እንዲሁም የኑሮ ጫናን በማቃለል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ዋነኛ ዓላማም ሸማቾች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻል ሲሆን፤ ገበያዎቹ ምርቶቹን ከአርሶ አደሮች፣ ከፋብሪካዎች ወይም ከሸማቾች የኅብረት ሥራ ማህበራት በቀጥታ በመረከብ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
ኢዜአ በመዲናዋ በሚገኙ የተለያዩ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ሸማቾችና ነጋዴዎች በገበያዎቹ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙና እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡት ሸማቾች መካከል አቶ አውላቸው ይልማ እንደገለጹት፤ የሚፈልጉትን ምርት በበቂና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ችለዋል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በአካባቢያቸው መከፈታቸው ለግብይት የሚያስፈልገውን ጊዜና የትራንስፖርት ወጪ እንደቆጠበላቸው ገልጸው፤ የገበያዎቹ በቅርብ ርቀት ተደራሽ መሆን ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የፈለጉትን ምርት እንዲያገኙ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሞልቶታል ጫንያለው በበኩላቸው፤ በመዲናችን አዲስ አበባ በየሳምንቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚያስተናግዱና ለከተማዋ ትልቅ እፎይታን የሚሰጡ የገበያ ስፍራዎች ሆነዋል ብለዋል፡፡
የቅዳሜና እሁድ የገበያ ማዕከላት የከተማዋን ነዋሪ የኑሮ ጫና ለማቅለል እና ገበያ ለማረጋጋት ትልቅ አቅም መሆናቸውንም ጠቅሰው ምርቶችን በቀጥታ ለህዝቡ እንዲቀርቡ በማድረግ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድም ገበያዎቹ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
መንግስት ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ ለማገናኘትና የኑሮ ውድነቱን ጫና ለማቃለል የወሰደው ይህ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ማቋቋም እርምጃ፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ እፎይታንና በጎ ምላሽን ያስገኘ መሆኑን ነጋዴዎችም ጭምር ጠቅሰዋል፡፡
በእሁድ ገበያ ላይ በመሳተፍ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የሚያቀርቡት እነኚሁ ነጋዴዎች፤ ከኅብረት ሥራ ማህበራት እና ከአቅራቢዎች በቂ ምርት እያመጡ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ከነጋዴዎቹ መካከል ዮርዳኖስ መልካሙ እንደገለጹት፤ ገበያው ምርታቸውን በቀጥታ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረስ በእጅጉ እየረዳቸው ይገኛል።
ለሸማቹ ማህበረሰብ ከመደበኛው ገበያ ባነሰ ዋጋ ምርቶችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ መንግሥት የገበያ ቦታዎችን በማመቻቸት ምርቶችን ከአቅራቢዎች በቀላሉ በማግኘት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ማስቻሉን አብራርተዋል።
ሌላኛው ነጋዴ መለሰ ካሳው በበኩሉ፤ ይህም ምርቶችን በበቂ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለማቅረብ እጅግ ጥሩ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስገንዝቧል።
ኅብረተሰቡ በእነዚህ መገበያያ ቦታዎች በመገኘት የሚፈልገውን ምርት በደስታና በእፎይታ እየገዛ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ነጋዴው አወቀ ቦልዲስ ናቸው፡፡
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በአካባቢያቸው በማገኘታቸው መደሰታቸውን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ የኅብረተሰቡን ፍላጎት ይበልጥ ለማሟላት የምርት አቅርቦቱን በስፋትና በጥራት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡