ቀጥታ፡

የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ከተወያየ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በቀዳሚነት የተወያየው፣ የሀረሪ ብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲን የሀረሪ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ በሚል ስያሜ እንደገና ለማቋቋም በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው።

ይህም የተቋሙን ሥልጣንና ተግባራት የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ተቋማት በአሁኑ ወቅት ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ ጋር ማጣጣም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሲሆን፤ ተቋሙ በብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ደረጃ ተደራጅቶ በብቃት፣ በጥራትና በውጤታማነት እንዲሠራ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።


 

ካቢኔው በረቂቅ አዋጁ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማከል፣ እንዲጸድቅ ለክልሉ ምክር ቤት መርቶታል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በሁለተኛነት የተወያየበት አጀንዳ፣ የፍልሰት ጉዳዮች አስተባባሪ ምክር ቤትና የትብብር ጥምረትን ለማቋቋም በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ያተኮረ ነበር።

ደንቡ ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳትና አግባብነት ያላቸውን አካላት ያቀፈ ክልላዊ የፍልሰት ጉዳዮች አስተባባሪ ምክር ቤትና የትብብር ጥምረትን በማቋቋም፤ በሰው የመነገድ እና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ እንዲሁም የወንጀል ድርጊቱን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚያስችል ተመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያግዝ አደረጃጀት በመፍጠር፣ የዜጎችን ተጋላጭነት የሚቀንሱ ተግባራትን ለማከናወንና ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝ ተገልጿል።

የመስተዳድር ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

ቀጥሎም ምክር ቤቱ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓትን ለማሻሻል በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት አድርጓል።

ደንቡ ቀደም ሲል ተግባራዊ በተደረገው ክልላዊ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሥርዓት የተጀመሩ አበረታች ሥራዎችን ማሻሻልን ያለመ ሲሆን፤ በተበታተነ መልኩ ሲተገበር የቆየውን አሠራር በተቀናጀ ሁኔታ በሁሉም የክልሉ የአስተዳደር እርከኖች አስተሳስሮ ለመምራት፣ እንዲሁም በክልሉ ሕብረተሰብ መካከል ያለውን የእርስ በእርስ የመደጋገፍ ባሕል በማጠናከር ፍትሐዊ፣ ጥራትና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የታለመ ነው።

ከዚህም በላይ በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አስፈጻሚ አካላትን ተግባርና ኃላፊነት በግልጽ በማስቀመጥ፣ የሀብት አሰባሰብ ሥርዓትንና ተጠያቂነት የሰፈነበት የፋይናንስ አጠቃቀምን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በዚህ ረቂቅ ደንብ ላይም በሰፊው ከተወያየ በኋላ ሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።


 

የካቢኔው የማጠቃለያ አጀንዳ የነበረው፣ የቱሪዝም ኮሚሽን ለማቋቋም በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ የመከረበት ጉዳይ ነው።

የሀረሪ ክልል በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ሁለት ቅርሶችን ጨምሮ፣ የበርካታ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት ናት።

የቱሪዝም ዘርፍ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተውን ድርሻ ለማሳደግ፣ በአዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማትና በኢኮ-ቱሪዝም ዘርፍ ውጤቶችን ለማስመዝገብ፣ ዘርፉን በተቀናጀና በባለቤትነት የሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል።

ለዚህም የቱሪዝም ዘርፉን በራሱ የሚመራ፣ ከበጀትና ከሰው ኃይል አስተዳደር አንጻር ተቋማዊ ነጻነት ያለው የቱሪዝም ኮሚሽን ማቋቋም የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የመስተዳድር ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም