18ኛው ዓመታዊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በይፋ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
18ኛው ዓመታዊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በይፋ ተከፈተ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 1/2018(ኢዜአ)፦18ኛው ዓመታዊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በይፋ ተከፍቷል።
ዓውደ ርዕዩ ከዛሬ ሰኔ 1 ቀን እስከ ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ከ40 በላይ የመጻሕፍት አከፋፋዮች፣አሳታሚዎችና የመጻሕፍት መደብሮች ተሳትፈውበታል።
በዚህ የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ በሁሉም የዕውቀት ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ በርካታ ነባርና አዳዲስ መጻሕፍት ለአንባቢያን በቅናሽ ዋጋ የቀረቡ ሲሆን አዳዲስ መጻሕፍትም ይመረቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ላለፉት ከ50 ዓመታት በላይ በርካታ መጻሕፍትን ሲያሳትምና ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት በሚያደርገው ጉዞም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስን አቅም የማሳደግና የዘመኑን ገበያ በመጠቀም ተደራሽነቱን የሚያሰፉ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዕውቀትን ለትውልድ የማሻገርና ተቋሙ ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።