የጠቅላላ ምርጫው ስኬት ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለዓለም ያስመሰከሩበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላላ ምርጫው ስኬት ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለዓለም ያስመሰከሩበት ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ስኬት ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለዓለም በድጋሜ ያስመሰከሩበት ትልቅ ሀገራዊ ሁነት መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስተጋቡ አሉታዊ ዘገባና ስሁት ምኞቶችን ያመከነ ታሪካዊ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ውሎ፤የድምፅ አሰጣጥ ባልተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎችም እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ ተካሂዶ ፍፃሜውን አግኝቷል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፥የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስተጋቡ አሉታዊ ዘገባና ስሁት ምኞቶችን ያመከነ ታሪካዊ ድል ነው።
በምርጫ ሂደቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ በመምረጥ መንግሥትን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መመስረት እንደሚችል በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ሥርዓትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ለዓለም ማስመስከሩን ተናግረዋል።
በውጭ ዓለማት ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎችም የዜጎች የምርጫ ንቁ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ባህል እያበበ መምጣቱን እንዳስገነዘበ አንስተዋል።
በተቃራኒው የኢትዮጵያን በጎነት የማይሹ ውስን አካላት ያስተጋቡት ከንቱ ጩኸት በኢትዮጵያዊያን የነቃ ተሳትፎ መምከኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በውጭ ሀገራትና የዲሞክራሲ ልምምድ በጎለበተባቸው ሀገራት የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ጥያቄ ጭምር እንደነበር አንስተዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የኢትዮጵያዊያን ንቁ ተሳትፎም የዲሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታና ልምምድን ዳያስፖራው ማህበረሰብ በአዎንታ እንደሚመለከተው ጠቅሰዋል።
በምርጫው ተሳትፎ ህዝቡ ለሀገር ግንባታና ሁለንተናዊ ዕድገት ያለውን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ለዓለም ህዝብ በተግባር ማሳየቱን አብራርተዋል።
በውጭ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸውን ብዝኅ የዕድገት ተስፋ በመመልከትና በመጎብኘት በተፈጠረው የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።