በኦሮሚያ ክልል በ240 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ፍራፍሬ እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በ240 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ፍራፍሬ እየለማ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በ240 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ፍራፍሬ እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በበጀት ዓመቱ 29 ሚሊዮን ኩንታል የፍራፍሬ ምርት መመረቱም ተገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የፍራፍሬ ልማት ዳይሬክተር አቶ ቻላቸው አዱኛ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በክልሉ ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ለፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት ምቹ የአየር ንብረት፣ በቂ የዝናብ መጠንና ተስማሚ የአፈር ዓይነት ያለው በመሆኑ ለዘርፉ ምርታማነት ከፍተኛ አቅም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የምግብ ስርዓትን ከማሻሻል ረገድ ሚናው የላቀ በመሆኑ በተሰሩት በርካታ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በዚህም የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እያደገ ነው ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ እንደ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ አፕል እና ሎሚ ያሉ ዋና ዋና የፍራፍሬ ዓይነቶች የዞኖቹን መልክዓ ምድርና የአየር ንብረት መሰረት በማድረግ በትኩረት እየለማ ነው ብለዋል።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ምርጥ ዘሮችን በመጠቀምና የማስፈጸም አቅምን በማሻሻል ልማቱ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዚህም በ2013 ዓ.ም ከ90 ሺህ ሄክታር ያልበለጠ የነበረው የፍራፍሬ ልማት፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 240 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በበጀት ዓመቱ 29 ሚሊዮን ኩንታል የፍራፍሬ ምርት መመረቱንም ተናግርዋል።
ከዚህ ውስጥም ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው የአቮካዶ ምርት መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት 2 ሺህ 400 ኩንታል የአቮካዶ ምርት ወደ ውጭ መላኩን አንስተው፣ ዘንድሮም በተሻለ ሁኔታ ለመላክ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቹ የግብርና ኤክስቴንሽን ፓኬጁን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የተለያዩ ሙያዊ ድጋፎችና ስልጠናዎች እየተሰጧቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።