የምግብ ጥራትና ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የላብራቶሪ አቅም እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ጥራትና ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የላብራቶሪ አቅም እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የምግብ ጥራትና ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የላብራቶሪ አቅም እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ገለጸ።
ባለሥልጣኑ ”ከምግብ ደህንነት ችግር ወደ መፍትሔዎች በሁሉም ቦታ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ” በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነት ቀን ምክንያት በማድረግ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የምግብ ደህንነት ችግር ሕፃናትን ጨምሮ ለዓለም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የጤና ጠንቅ ነው።
በኢትዮጵያ በምግብ ደህንነት መጓደል የሚከሰትን የጤና እክል ለመቀነስም የላብራቶሪ አቅምና የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከር የምግብ ዝግጅት አቅርቦት ሰንሰለቶችን ማጠናከር የሚያስችል የድጋፍና ክትትል እንዲሁም የቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የምግብ ጥራትና ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የላብራቶሪ አቅም እየተገነባ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ መድረኩም የምግብ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ነው ብለዋል።
በቀጣይም ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ በማድረግ የቁጥጥር፣ የምግብ ስታንዳርድና የጥራት ላብራቶሪ አቅም የመገንባት ስራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነት ቀን በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ8ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።