ቀጥታ፡

በክልሉ በሚቀጥሉት የክረምት ወራት የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለመኸር እርሻ አመች ነው

ጋምቤላ፤ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በሚቀጥሉት የክረምት ወራት የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለመኸር እርሻው አመች መሆኑን በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለ2018 ዓ.ም የክረምት ወቅት ያወጣው ትንበያ እንደሚያሳየው፣ በዘንድሮው መኸር የሚኖረው የዝናብ ስርጭት መደበኛና ለአዝመራው አመቺ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

ይህ መረጃ ክልሉ ካለው ሰፊ የሩዝ፣ የበቆሎና የጥራጥሬ ሰብሎች ልማት አቅም አንጻር አርሶ አደሩና የኢንቨስትመንት አካላት አስቀድመው እንዲዘጋጁ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።

የጋምቤላ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሚቀጥሉት የክረምት ወራት የሚኖረው ዝናብ መደበኛና ብዙ ከመደበኛ ያላለፉ የዝናብ ስርጭት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በክልሉ የሚኖረው የዝናብ ስርጭት በአብዛኛው መደበኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመኸር እርሻው መሳለጥ ዓይነተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተለይም አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ የግብርና ልማቱን ለማከወንና ለመከታተል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር መሪ ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።

በአንፃሩ የዝናቡ ዝርጭት በአብዛኛው መደበኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ የወባ በሽታ ሊጨምር ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

እንዲሁም አልፎ-አልፎ በሚኖረው ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት ቅጽበታዊ ጉርፍ ሊከሰት ስለሚችልም ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ  አቶ ተስፋሁን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም