ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለሃብቶች በገበያ ማረጋጋት ሂደት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ አግዟል 

ደሴ፤ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገላቸው ድጋፍ ምርታማነታቸውን በማሳደግ በገበያ ማረጋጋት ሂደት ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ባለሃብቶች ገለጹ።

በአማራ ክልል ከ414 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱንም የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል።

በባህር ዳር ከተማ "የአለማየሁ ሀይማኖት ዘይት ፋብሪካ" ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ እሱባለው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለማግኘት አግዟል።

በንቅናቄው የነበረባቸው ችግር መፈታቱ ምርታማነታቸው እንዲያድግና ገበያ በማረጋጋት ሂደት የድርሻቸውን እንዲወጡ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ባገኙት ድጋፍ የዘይት ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ወደማምረት ሥራ መግባቱን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፣ በቀን ከ20 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት በማምረት ለህብረተሰቡ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው በኮምቦልቻ ከተማ የ"ይመር አሊ ዱቄትና ብስኩት ፋብሪካ" ተወካይ አቶ ደረጀ ገብሬ በበኩላቸው፣ መንግስት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ በሰጠው ትኩረት የፋብሪካው ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

"በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተደረገልን ድጋፍ ተኪና ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት እንድንችል አድርጎናል" ያሉት ባለሃብቱ፣ ፋብሪካው ከውጭ ይገባ የነበረን የብስኩት ምርት በሀገር ውስጥ በማምረት መተካቱን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ዓመታት የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲነቃቃ ማድረጉን ገልጸዋል።

ለዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 414 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 3 ሺህ 518 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን በማሳያነት አስረድተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

ችግሮች በቅንጅት እንዲፈቱ፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታማነት እንዲጨምር፣ ገበያውን እንዲያረጋጉና ተጠቃሚ እንዲሆኑም ማስቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም የኤሌክትሪክ ኃይል እና የመሬት አቅርቦትን  ጨምሮ የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የአማራ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መድረክ ትናንት በኮምቦልቻ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም