ቀጥታ፡

በዓለም አቀፍ ውድድሮች የቀጠለው የኢትዮጵያ አትሌቶች ድል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ድል ማስመዝገባቸውን ቀጥለዋል።

በብራዚል በተካሄደው የሪዮ ዴ ጃኔይሮ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ድል ሲቀዳጁ፣ በስቶኮልም ዳይመንድ ሊግ ደግሞ አትሌት ብርቄ ሓየሎም አሸናፊ ሆናለች።

ዛሬ በተካሄደው የዘንድሮው የሪዮ ዴ ጃኔይሮ ማራቶን ውድድር፣ በሴቶች አትሌት ጋዲሴ ሙሉ 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ አሸናፊ ሆናለች።


 

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ በአጠቃላይ በመቆጣጠር ፍጹም የበላይነታቸውን አሳይተዋል።

አትሌት ትርፌ ፀጋዬ 2ኛ፣ አትሌት አዝመራ አብረሃ 3ኛ፣ አትሌት አፍራ ጉዳፈይ 4ኛ እና ዝናሽ ደበበ 5ኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል።

በወንዶች አትሌት ፀጋዬ ጌታቸው በአስደናቂ አጨራረስ ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቋል።

ፀጋዬ ውድድሩን ለመጨረስ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ የወሰደበት ሲሆን፣ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አንተንአየሁ ይስማ በሴኮንድ ልዩነት ተበልጦ ሁለተኛ መሆን ችሏል።


 

በሌላ በኩል በስዊድን ስቶኮልም በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር አትሌት ብርቄ ሓየሎም በ1500 ሜትር አሸንፋለች።

ብርቄ ከሁለት ቀናት በፊት በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደው ተመሳሳይ የርቀት ውድድር በአንደኝነት ማጠናቀቋ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በአጭር የሰዓታት ልዩነት 4:00.68 በስቶኮልም ዳግም በማሸነፍ አስደናቂ ብቃቷን አሳይታለች።

በዚሁ ውድድር ላይ የተካፈለችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሐረገወይኒ ካላዩ ውድድሩን አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም