ቀጥታ፡

የተገልጋይ እንግልትን ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ተግባራዊ ሆኗል

አዳማ፤ ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ):- በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ሕገወጥነትና የተገልጋይ እንግልት ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥ ተግባራዊ መደረጉን የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው አዲስ ተግባራዊ ባደረገው ‘ኦሮ ዲጂታል ቲኬት’ አገልግሎት እና ዘርፉን ለማዘመን እየተከናወኑ ባሉ የሪፎርም ሥራዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል።




የኤጀንሲው ኃላፊ ከማል ማሜ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ምቹ፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ያለመ ‘ኦሮ ዲጂታል ቲኬት አገልግሎት’ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

ዘመናዊ አሠራሩ በዘርፉ ሲስተዋል የነበረን ብልሹ አሠራር፣ የመልካም አሥተዳደር እጦትና የተጋልጋዮችን እንግልት በመከላከል ተጨባጭ ውጤታ እያመጣ መሆኑንም አመላክተዋል።

በመናኸሪያና በአካባቢው የሚስተዋሉ ሕገወጥ ተግባራትን ለማስቀረት የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማኅበራትና የቦርድ አመራሮች ያለቸው ሚና የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል።




በአሁኑ ወቅት ከ17 ሺህ በላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ ዲጂታል ሲስተሙ መግባታቸውን የገለጹት ደግሞ በኤጀንሲው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዳይሬክተር ሙስባሁዲን አብዱልመጂድ ናቸው።

በቴክኖሎጂ የተደገፈው አሠራር በስምሪት ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎችን ለመለየት፣ ከመናኸሪያ ውጪ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ተከታትሎ ለመቅጣት፣ ያለአግባብ የስምሪት መውጫ መስጠት ችግርን ለማስቅረት እና አገልግሎት አሰጣጡን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ለማድረግ የጎላ ጥቅም እንዳለውም አስረድተዋል።



የኦሮሚያ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ማኅበራት የቦርድ ሰብሳቢ ታምራት በየነ በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው የጀመረው የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ሥራ የተሽከርካሪ አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣምና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም