ቀጥታ፡

የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት መዘመን ለህብረተሰቡ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አስችሏል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት መዘመን ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እንዳስቻላቸው ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡ 

መንግስት በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ እያደረጋቸው ያሉ ሁለንተናዊ ማሻሻያዎችና በመዲናዋ የተገነቡት ዘመናዊ የአውቶብስ ፌርማታዎች ለአገልግሎቱ መቀላጠፍና ለተሳፋሪዎች ምቾት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ 

በመዲናዋ ደረጃቸውን በጠበቁና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ለማህበረሰቡ የተሳለጠ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ገቢራዊ ተደርጓል፡፡

በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች ሳምንቱን ሙሉ ያለማቋረጥ የትራንስፖርት አገልግሎት በማቅረብ ላይ ያሉት የከተማ አውቶብሶች ለነዋሪዎች ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ እፎይታን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ መኮንን ለገሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የብዙሃን ትራንስፖርት ከሌሎች አማራጮች አንጻር አነስተኛ ታሪፍ ያለው በመሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡

የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይሄውም ያለ ምንም እንግልት በሰዓታቸው የሥራ ቦታቸው ላይ እንዲገኙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ገቢያቸውን ያማከለና ተመጣጣኝ የትራንስፖርት አገልግሎት ከማግኘት ባለፈ ለሥራቸው መቃናትና ምርታማነት የጎላ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ መስከረም ዳመነ፤ አገልግሎቱ በየጊዜው እየተሻሻለ በመምጣቱ ጠዋትም ሆነ ማታ ፈጣን፣ ምቹና ቀልጣፋ ግልጋሎት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት መዘመን የነዋሪዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ በማሳለጥ ገንቢ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የከተማ አውቶብስ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገው አዲሱ አሠራር በሥራቸው ላይ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ 


 

አቶ ያለው ነጋ በትራንስፖርት ዘርፉ የተተገበረው ሪፎርም በካሜራና ጂፒኤስ (GPS) የታገዘ ዘመናዊ አሰራርን በማምጣት የአሽከርካሪዎችን የቴክኖሎጂ አቅም ማሳደጉን ገልጸዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ቀደም ሲል በፌርማታዎች ይስተዋሉ የነበሩትን ሰልፎች በማስቀረት በመዲናዋና ከዙሪያ ከተሞች ለሚመጡ ተጠቃሚዎች ተመራጭ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ሌላኛዋ አሽከርካሪ ወይዘሮ ፍሬህይወት ኤካ፤ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት መዘመን በተለይ ርቀት ላላቸው መስመሮች ከታሪፍ አንፃር እጅግ አዋጭ ነው ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም