7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የተያዘው ዕቅድ በስኬት የተፈፀመበት ነው -አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የተያዘው ዕቅድ በስኬት የተፈፀመበት ነው -አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሀገራዊ ግቦቹን እንዲያሳካ እና ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ በብልጽግና ፓርቲ የተያዘው ዕቅድ እና የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት በስኬት የተፈፀሙበት መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ላለፉት ሁለት ቀናት በሶማሌ ክልል ሸቤለይ ሪዞርት ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር እስከ ምርጫው ዕለት ያለውን የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ሥራዎች ዕቅድ አፈፃፀም በጥልቀት በመገምገም እና የድህረ ምርጫ ሥራዎች ላይ በመግባባት መድረኩ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ለምርጫው ስኬታማነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፌዴራል እና የክልል ፀጥታ ኃይሎች፣ በታዛቢነት የተሳተፉ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ተቋማት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፅኑ ቁርጠኝነት በማሳየት ከለሊቱ 10 ሰዓት እስከ ሚቀጥለው ለሊት 10 ሰዓት ድምፅ ለመስጠት የተሰለፈው እና ለምርጫው ስኬት የሚችለውን ሁሉ ላደረገው ለተከበረው ሕዝብ፣ እንዲሁም ሌሎች አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናችንን አቅርበዋል።
ከግምገማዊ ውይይት መድረኩ ጎን ለጎን፣ የስብሰባው ተሳታፊ ከፍተኛ አመራሮች በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ በጅግጅጋ እየተከናወኑ ያሉ ዐበይት የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በክልሉ መንግሥት እና በሕዝቡ ጥረት እየተመዘገቡ ያሉ አንጸባራቂ ስኬቶችን በተጨባጭ መመልከታቸውን ነው የገለጹት።
የጅግጅጋ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የቀየሩ፣ የተቀናጁ መሠረተ ልማቶችን ያሟሉ እና ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የፈጠሩ ናቸው ብለዋል አቶ አደም።
ይህ ሥራ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን እና ከተማዋን የቀጣናው የልማት እና የንግድ ማዕከል እንድትሆን እንዳደረጋትም ጠቁመዋል።
በክልሉ መንግሥት ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃውን አዲስ የፖሊስ ሆስፒታል ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚሰጠው አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተለይም የፖሊስ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው የሚያገኙትን የጤና አገልግሎት በማላቅ፣ የፀጥታ ኃይሎች ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በላቀ ሞራል እና ቁርጠኝነት እንዲወጡ የሚያግዝ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ትኩረት የሕዝብን አገልጋይነት ማረጋገጥ እና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ነው ያሉት አቶ አደም ፋራህ፣ በመላው ኢትዮጵያ የተገነቡት እና ግንባታቸው እየተጠናቀቀ ያሉት የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት የቢሮክራሲ ማነቆዎችን በመቅረፍ የዜጎችን እርካታ በከፍተኛ ደረጃ እያሳደጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በጅግጅጋ የተመለከቱት ፈጣን እና ሁለንተናዊ ለውጦች የብልጽግና ፓርቲን የልማት እና የመልካም አስተዳደር እሳቤዎች እንዲሁም ፖሊሲዎች ውጤታማነት በተግባር ያረጋገጡ መሆናቸውን አስምረውበታል።
ከተማዋ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች ያለችበት አግባብ እጅግ የሚያስደስት፣ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ምሥል ያየንበት እና ለሌሎች አካባቢዎችም አርአያ የሚሆን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በከፍተኛ ትጋት እና ቁርጠኝነት እውነተኛ ዴሞክራሲን ከተጨባጭ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የሰላም ስኬቶች ጋር በማጣመር፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በተግባር የማረጋገጥ ስኬታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።