በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን ለጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን ለጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተዋል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ)፡-በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን ለጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየታቸውን የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን፤ የድምፅ አሰጣጥ ባልተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎችም እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ መካሄዱ ይታወቃል።
ኢትዮጵያዊያን በመረጡበትና ኢትዮጵያም ባሸነፈችበት ምርጫ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ አስተምህሮና ታዛቢነት የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል።
የምርጫ ሂደቱን በማስመልከትም የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽንና የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር የሥራ ኃላፊዎች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን እንዳሉት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማስፈጸም አቅም በተግባር የታየበት ነው።
በምርጫውም በምርጫ አስተምህሮና ታዛቢነት በርካታ አባላትን በማሰማራት የሂደቱን ዴሞክራሲያዊነትና አሳታፊነት ማረጋገጥ የሚያስችል ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።
በዚህም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያዊያንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና በሁሉም መለኪያ የነቃ ተሳትፎ ያደረጉበት መሆኑን መታዘብ እንደተቻለ ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያዊያንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ መሰረት በመጣል ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ያሳዩበት መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሰከነ ተሳትፎ የታየበትና ሰብዓዊ መብቶችን ያከበረ ነበር ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ ሃሳባቸውን ለህዝብ ባቀረቡበት ወቅት የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጨምሮ በብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ትብብር አስደማሚ እንደነበር መታዘባቸውን ገልጸዋል።
በምርጫ ወቅት በነበረው ትዝብትም ምርጫ ጣቢያዎች ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መራጮች ምቹና ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በተሟላ ሁኔታ የተጠቀሙበት ሁኔታን ፈጥሮ እንዳለፈ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የዘንድሮው የምርጫ ሂደት ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አንጻር በጥሩ ደረጃ ላይ የተከናወነና ስኬታማ እንደነበር አስታውቀዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወጣቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በተግባር በመጠቀም የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል ያለው ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ተወካይ አሌክሳንደር ንጉሴ ነው።
በምርጫ ሂደቱ የነበረው የወጣቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የነቃ ተሳትፎም ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ወሳኝ መድረክ መሆኑን ገልጿል።
በሂደቱ የፌዴሬሽኑ ታዛቢዎች ከተለያዩ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተወካዮች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ከምርጫ አስፈፃሚዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንደተወጡ ተናግሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት እናታለም እንዳለ በበኩላቸው፤ በምርጫው ሂደት ሴቶች የነበራቸው ንቁ ተሳትፎ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝት በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።
በሂደቱም በርካታ ሴቶች በምርጫ ታዛቢነትና በመራጭነት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ የመምረጥ መብታቸውን በተግባር እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደተቻለ አስረድተዋል።