የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን የሚተኩ እና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች በስፋትና በጥራት እንዲመረቱ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን የሚተኩ እና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች በስፋትና በጥራት እንዲመረቱ አስችሏል
ኮምቦልቻ ፤ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካትና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚሆኑ ምርቶችን በጥራትና በስፋት በማምረት ረገድ ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለፁ።
«ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት» በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የአማራ ክልል ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በኮምቦልቻ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ ንቅናቄው ባለፉት ዓመታት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ከፍተኛ ሚና አበርክቷል።
ሚኒስትሩ አክለውም፣ በንቅናቄው አማካኝነት ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ፣ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና በተግዳሮቶች ላይ መፍትሔ መስጠት መቻሉን ገልጸው፤ በእነዚህም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ንቅናቄው የገቢ ምርቶችን ከመተካትና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ከማምረት ባሻገር፣ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ማስቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአማራ ክልልም ንቅናቄው በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩና አዳዲስ ባለሃብቶችም በኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፤ በክልሉ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ንቅናቄው የገቢ ምርቶችን በመተካትና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ረገድ ካስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር፣ ማኅበረሰቡ በሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀምና በራሱ ምርት የመኩራት ባሕል እንዲያዳብር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ዘርፉን የመደገፍ፣ የማዘመንና የማስፋት ሥራዎችን በማጠናከር ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም የክልሉ መንግሥት ለዚህ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፤ በንቅናቄው አማካኝነት ባለፉት አራት ዓመታት 496 የሚሆኑ አዳዲስና ነባር ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ሥራ እንዲሸጋገሩ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ከ125 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
አቶ እንድሪስ አክለውም፤ በንቅናቄው አማካኝነት ከባለሀብቶች ጋር በቅርብ በመሥራት ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የብድር አቅርቦት እንዲያገኙ፣ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸው እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያገኙ መቻሉን ገልጸዋል።
በመርሐግብሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮች፣ ባለሃብቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።