ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሰመራ፣ግንቦት 30/2018(ኢዜአ):-ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና ፍልሰትን ለመግታት የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎችንና የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሕግና ማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኖች ገለጹ።
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ደግሞ በታዳጊ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሰብአዊ ጉዳቶችን እያስከተለ የሚገኝ አሳሳቢ ክስተት ነው።
ኢትዮጵያም የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደመሆኗ መንግሥትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ችግሩን ለመግታት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላቸውን የምርምር አቅምና የማኅበረሰብ አገልግሎት ድርሻ በመጠቀም፣ የሕገ-ወጥ ዝውውርን መነሻ ምክንያቶች ለይቶ ማውጣትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ላይ ሰፊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይታመናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሕግና ማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኖች እንደገለጹት፤ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና ፍልሰትን ለመግታት የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎችና የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የህግና ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኀላፊ ቹዌል ኦኬደ እንዳሉት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰትን ከመከላከል አኳያ የተለያዩ ተግባራት በቅንጅት ተከናውነዋል።
ስልጠናዎችን በማዘጋጀት በአካባቢው በሚገኙ አምስት ቋንቋዎች ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ኃላፊ አቶ አብርሃም ክንፈ፤ ዩኒቨርሲቲው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና ፍልሰትን ለመከላከል ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነፃ የሕግ ድጋፍና የማማከር አገልግሎት መስጠቱን አስታውቀዋል።
ማዕከላቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሕግ ቢሮዎችን በመክፈት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና ፍልሰትን ለመግታት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ተጎጂዎች የሕግ ውክልና እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን የተመለከቱ ተግባራትን የማስተባበር ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የህግና ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኀላፊ ሳለአምላክ አታላይ እንዳሉት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።
የምርምርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀትና የህግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
መንግሥት መደበኛ ያልሆነ የዜጎችን ፍልሰትና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስቀረት፣ ዜጎች ሕጋዊ አሠራርን ተከትለው መሥራት የሚችሉበትን ዕድል እያመቻቸ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዘካሪያስ ኤርኮላ(ዶ/ር) ናቸው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሚመራበትን ሕግ እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴር ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና ድንበር ማሻገርን መከላከል የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ሕጎችን አውጥተው ወደ ተግባር መግባታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡፡
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነትና ከፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተሰናዳው አህጉር አቀፍ ሲምፖዚየም ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
ሲምፖዚየሙ "ሕገ-ወጥ ፍልሰት እና የሰዎች ዝውውር፤ የሕግ፣ ማኅበራዊ እና ተቋማዊ አመለካከቶች" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ ነው።