ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በስኬት የተካሄደና የሰከነ የፖለቲካ ፉክክር የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በስኬት የተካሄደና የሰከነ የፖለቲካ ፉክክር የታየበት ነው
አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ)፡-ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በስኬት የተካሄደና የሰከነ የፖለቲካ ፉክክር የታየበት መሆኑን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ገለጸ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ውሎ፤ የድምፅ አሰጣጥ ባልተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎች እስከ ዕኩለ ለሊት ድረስ ተካሂዶ ፍፃሜውን አግኝቷል።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያም አሸንፋለች።
ይህን ተከትሎም በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ስር የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን ይፋ እያደረጉ ሲሆን፤ ዜጎችም ጊዜያዊ ውጤቶችን እየተመለከቱ እንደሚገኙ ቦርዱ አስታውቋል።
በምርጫ ሂደቱም በርካታ የሀገር ውስጥ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ አስተምህሮና ታዛቢነት፣ የኢጋድና የአፍሪካ ህብረት ልዑካን ደግሞ በምርጫ ታዛቢነት ስኬታማ ተሳትፎ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዘንድሮው ምርጫ ዜጎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ቆርጠኝነታቸውን አሳይተዋል።
በምርጫ ፉክክር ሂደቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ ሃሳባቸውን ለህዝብ ሲያቀርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ስልታዊ ትብብር አስደማሚ እንደነበር መታዘባቸውን ገልጸዋል።
ይህም ፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጨምሮ ለሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅሞች መከበር የሰከነ የፖለቲካ ምኅዳር በመፍጠር እየተሳተፉ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል።
በምርጫ ወቅት በነበረው ትዝብትም ምርጫ ጣቢያዎች ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መራጮች ምቹና ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በተሟላ ሁኔታ የተጠቀሙበት መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች፣ መስማት ለተሳናቸው፣ ነፍሰ ጡሮችና ጨቅላ ሕፃናት ለያዙ ወላጆች የተፈጠረው አስቻይ ምኅዳር ለመራጮች ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ እንዳለፈ ገልጸዋል።
በሌላ መልኩም የዘንድሮው የምርጫ ሂደት ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አንጻር በጥሩ ደረጃ ላይ የተከናወነና ስኬታማ እንደነበር አስታውቀዋል።