ቀጥታ፡

የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅና ለማስከበር የትኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን-ተመራቂ ወታደራዊ መኮንኖች

ድሬደዋ፣ግንቦት 30/2018(ኢዜአ)፦በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት ዘመናዊ ወታደራዊ ሙያና ጥበብ በመታገዝ፣የሀገርን ሉዓላዊነትን ለማስከበር የትኛውንም ዓይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ከሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተመራቂ ወታደራዊ መኮንኖች ተናገሩ።

የሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን የ27ኛ ዙር ፅናት ኮርስ ዕጩ መኮንኖች በትናንትናው እለት አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በትምህርት ቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ዕጩ መኮንኖች ማዕረግ አልብሰዋል።


 

ከተመራቂዎቹ መካከል ምክትል መቶ አለቃ ዘካሪያስ አባተ እንደገለጹት፤ በትምህርት ቤቱ ያገኙትን ዘመናዊ ሥልጠናና የዳበረ ልምድ በመጠቀም፣ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የተጣለባቸውን ማንኛውንም ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው።

በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ላይ በመሰማራት የሀገርንና የዜጎችን ጥቅም አስከብረው ማገልገላቸው፣ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት የመፈጸም ትልቅ ልምድ እንዳስገኘላቸው የገለጹት ደግሞ ሌላው ተመራቂ መኮንን ምክትል መቶ አለቃ ታደለ ናኒዮ ናቸው።


 

በማሰልጠኛ ቆይታቸው የተሰጣቸው ወታደራዊ የተግባርና የንድፈ-ሐሳብ ሥልጠና፤ ወደፊት የሚጠብቋቸውን ቀጣይ ተልዕኮዎች በላቀ ብቃትና ጀግንነት ለመወጣት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

ምክትል መቶ አለቃ ማስተዋል በለጠ በበኩላቸው፥ ሴት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በማናቸውም ፈተና ውስጥ ሆነው በታላቅ ጀግንነትና ብቃት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር፣እንዲሁም የዜጎችን ደኅንነትና ከፍታ ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ምክትል መቶ አለቃ ሄዋን አማንም፤ ወደ አመራርነት መሻገር ትልቅ ሀገራዊና የሕዝብ ኃላፊነት መሸከም መሆኑን አስታውሰዋል።


 

ሀገራቸውን ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ለመጠበቅ እንዲሁም የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ከፍታ በፅናት ለማረጋገጥ የትኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አስምረውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም