ቀጥታ፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በንቃት የተሳተፉበት ምርጫ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ)፡-ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በንቃት የተሳተፉበት ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንደነበር የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት እናታለም እንዳለ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ያካሄደችውን ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የአፍሪካ ሕብረት፣ ኢጋድና የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ተከታትለውታል፡፡

ምርጫውን ከታዘቡት 55 የሀገር ውስጥ ሲቪክ ማህበራት መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ነው፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት እናታለም እንዳለ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ምርጫ ዜጎች መብታቸውን ተጠቅመው የሚበጃቸውን ፓርቲ የሚመርጡበት የዴሞክራሲ መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የሁሉም ማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶች ንቁ ተሳትፎ የተረጋገጠበት የፖለቲካ አውድ ነበር ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ በመውሰድ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በጠቅላላ ምርጫው ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበትን የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ሺህ በላይ አባላትን በማሰልጠን በዕለቱ የምርጫ ታዛቢዎችን መመደባቸውን ገልጸው፤ በርካታ ዜጎች የመራጭነት ካርድ በመውሰው ድምጽ ሰጥተዋል ብለዋል፡፡

ዜጎችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሰላማዊ፣ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ድምፅ መስጠታቸውን በማንሳት፤የህዝቡን ተነሳሽነትና ፍላጎትም አድንቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር በ1990 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም