ቀጥታ፡

በክልሉ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በበጀት ዓመቱ 158 መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደማምረት ገብተዋል-ቢሮው

ኮምቦልቻ፤ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በበጀት ዓመቱ 158 መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ማምረት መጀመራቸው ተገለጸ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሃግብር በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የነበሩ ችግሮችን እየፈታ መጥቷል።

በተለይም ባለሃብቱ ያነሳቸው የነበሩ የማስፋፊያና የአዳዲስ ኢንቨስትመንት ቦታዎች ጥያቄን፣ የብድርና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ማስቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ከማስፋፋት ባሻገር የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት እያገዘ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ወራት ብቻ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄው 158 መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ማምረት መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

የፌደራልና የክልሉ አመራሮቹ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን በቀጣይም ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

"ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው በዚህ መርሃግብር ላይ 145 ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም