በምስራቅ ቦረና ዞን ከ16 ሺህ በላይ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ለነዋሪዎች ተሰራጨ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን ከ16 ሺህ በላይ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ለነዋሪዎች ተሰራጨ
ነገሌ ቦረና፣ ግንቦት 30/2018 (ኢዜእ):-በምስራቅ ቦረና ዞን ቆላማ ወረዳዎች ከ16 ሺህ በላይ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር መሰራጨቱን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ ገዛሀኝ ኪታባ በዞኑ የወባ በሽታን ለመከላከል ለአካባቢ ንጽህናና ቁጥጥር ሥራዎች ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በተለይ ህብረተሰቡን በዘመቻ በሚከናወኑ የአካባቢ ንጽህና ጥበቃ ሥራዎች ላይ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የግልና የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን ለማሳካትም ለ67 ሺህ 381 ዜጎች የግንዛቤ ማሰጨበጫ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ስርጭት በዞኑ ጉሚ ኤልደሎ እና ሊበን ወረዳዎች ባሉ 11 የገጠር ቀበሌዎች መካሄዱን አቶ አቶ ገዛሀኝ አስታውቀዋል፡፡
የተሰራጨው አጎበርም 31ሺህ 639 የአርብቶ አደር ቤተሰብ አባላትን ከወባ በሽታ ለመከላከል የሚያስችል ነው ብለዋል።
የአልጋ አጎበሩ በፌደራል መንግስት የቀረበ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ ከ9 ሚሊዮን 660 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ከአጎበር ሥርጭቱ ጎን ለጎን ለወባ በሽታ መራቢያ ምቹ በሆነ 241 ሺህ 841 እስኩየር ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የጸረ ወባ መድሀኒት እርጭት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በየዓመቱ በዞኑ የወባ በሽታ በሚቀሰቀስባቸው ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 108 ቀበሌዎች ውሃ ባቆሩ አካባቢዎች የወባ መከላከያ ኬሚካል እርጭት መካሄዱንም ጠቁመዋል፡፡