ቀጥታ፡

በ19ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌት ጌታቸው ማስረሻና አትሌት መሰለች አለማየሁ አሸነፉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ)፦ 19ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ዛሬ ረፋድ ላይ መነሻ እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ተካሂዷል።

በወንዶች ውድድር የሸገር ሲቲው አትሌት ጌታቸው ማስረሻ አንደኛ በመውጣት በድል አጠናቋል።

ባየልኝ ተሻገር ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ፣ በላይ ጥላሁን ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ክለብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በሴቶች የአዲስ አበባ ፖሊሷ መሰለች አለማየሁ አሸናፊ ሆናለች።

ዝማም ባራኪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ የሸገር ሲቲዋ በቀለች ተኩ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

በ19ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን 455 እና በሴቶች 183 በድምሩ 638 አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የውድድሩ ዋና አላማ በዴንማርክ ኮፐንሃገን በመስከረም ወር 2019 ዓ.ም ለሚካሄደው 26ኛው የዓለም አትሌቲክስ የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች መምረጥ እና ተተኪዎችን ማፍራት ነው።

በውድድሩ ላይ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች የገንዘብ፣ሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የዘንድሮው ውድድር ተሳታፊዎች ብዛት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ434 አትሌቶች ጭማሪ ማሳየቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።

#ኢዜአ #Ethiopian_News_Agency

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም