በአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት አካል የሆኑ አዳዲስ የአስፋልት መንገዶች እየተገነቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት አካል የሆኑ አዳዲስ የአስፋልት መንገዶች እየተገነቡ ነው
አሶሳ፤ ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ)፦ በአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት አካል የሆኑ አዳዲስ የአስፋልት መንገዶች እየተገነቡ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሙሐመድ አልማሂ ገለጹ።
በዚህም መሠረት ከአሶሳ ሕዳሴ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ከተማዋ የሚያስገባው የአስፋልት መንገድ ግንባታ መጠናቀቁን ኃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።
እስከ 22 ሜትር ስፋት ያለው ይህ መንገድ 1 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም ጠቁመው፤ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ከማስቀረቱም ባሻገር ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንደሆነ አስረድተዋል።
በተያያዘም በከተማዋ በሌላኛው አቅጣጫ 4 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን አመላክተዋል።
የአስፋልት መንገዶቹ ግንባታ በአዲስ መልክ ባለሁለት መስመር መንገድ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሁለት አቅጣጫ እየተገነቡ የሚገኙት የአስፋልት መንገዶቹ የከተማዋን ዕድገት ታሳቢ ያደረጉ፣ የኮሪደር ልማትን ያካተቱ እና ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአስፋልት መንገዶችን በመጠገን ለአገልግሎት ክፍት የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።