ባሳለፍነው ሳምንት … - ኢዜአ አማርኛ
ባሳለፍነው ሳምንት …
ባሳለፍነው ሳምንት …
ከግንቦት 23 እስከ ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል …
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ
ባሳለፍነው ሳምንት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተካሂዷል።
ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመራጮች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምርጫው ወቅት ድምጽ ስለሰጡ መራጮች ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስደናቂም ተአምረኛም ሕዝብ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፈጣሪ በቀር ሕዝባችንን አሟልቶ ሊያውቅና ሊገመግም የሚችል ማን ነው? የዳበረ ባህል፣ ሀገር ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል ሕዝብ መሆኑን በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለዓለም አሳይቷል ብለዋል።
ማገልገል መታደል መሆኑን ገልጸው፤ ተመራጮች ያከበራችሁን አክብራችሁ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ዋጋ የከፈለውን ይህንን ሕዝብ በንጽሕና ለማገልገል ያብቃችሁ ሲሉም አስገንዝበዋል።
ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም የመልሶ ማልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት
ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለውን የመልሶ ማልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 22 ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማትን ይሸፍናል።
ይህ ፕሮጀክት የማይቆራረጥ የልማት ሥራችን ኅያው ምስክር ከመሆኑም በላይ የሀገራዊ ዕድገታችን፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የከተማ እድሳት በተግባር የታየበት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ጋር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩትና 73 አባላት ከያዘው የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ጋር መክረዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ ለዲሞክራሲ ግንባታ ሂደታችን ላበረከቱት አገልግሎትና አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋናችንን እናቀርባለን ብለዋል።
ዲሞክራሲያዊ ሂደቶች ከአኅጉራችን ነባራዊ ሁኔታና ተሞክሮ ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ለማድረግ አፍሪካዊ ተቋማት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።
የምርጫ ሂደታችንን ለመደገፍ በመላው ሀገሪቱ ታዛቢዎችን በማሰማራት የምርጫ ታዛቢ ልዑኩ ላደረገው ያልተቆጠበ ጥረት እውቅና እና አድናቆት እየሰጠን፤ የምልከታውን የተሟላ ውጤት እንጠብቃለን ሲሉም አመላክተዋል።
የወንዝ ዳርቻዎችን ከማስዋብ ያለፈ ፋይዳ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት፤ የወንዝ ዳርቻዎችን ከማስዋብ ያለፈ ፋይዳን የያዘ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ እንዲሁም ከእንጦጦ እስከ ቀበና ባለው መስመር የሚከናወነው መጠነ ሰፊ የከተማ ትራንስፎርሜሽንም፤ ከወንዞቹ ባሻገር እስከ 50 ሜትር የሚዘልቅ መሆኑን አስረድተዋል።
የአረንጓዴ ኮሪደሮችን፣ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን እና የንግድ ቦታዎችን ልማት ማካተቱን ጠቅሰው፤ ከተማዋን በእጅጉ የቀየረ ነው ብለዋል።
የወንዝ ዳርቻዎችን ገጽታ እና አገልግሎት ከማሻሻል ባለፈ በኮንስትራክሽን፣ በኢንጂነሪንግ፣ በመልክዓ-ምድር ውበት ግንባታ፣ በሎጂስቲክስ እና በተያያዙ ዘርፎች ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።
አብዛኛው ሥራ በሀገር ውስጥ መሐንዲሶች መቀረጹና መተግበሩ፤ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በከተማ ልማት እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ያላቸው ዐቅም እያደገ መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት።
ቀደም ሲል መርዛማ ኬሚካሎች እና ቆሻሻዎች የሚጣሉባቸው፣ በወንዝ ዳርቻዎች በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ የጎርፍ አደጋ ይጋርጡ የነበሩት እነዚህ አካባቢዎች፤ አሁን ላይ ወደ አረንጓዴ፣ ጤናማ እና ለሕይወት ምቹ ወደሆነ የከተማ ቦታነት እየተቀየሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም፤ የንግድ እና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ተቀናጅተው መገንባታቸው፤ የአካባቢ ጥበቃ እና የኢኮኖሚ ዕድገት ከዚህ ቀደም ከነበረው ያልተናበበ ሥራ ተላቀው በጥናትና በጋራ ግብ ተባብሮ መሥራት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ስለመሆኑ አመላክተዋል።
ይህ ፈጣን የልማት ሥራ አዲስ አበባን አረንጓዴ፣ ይበልጥ የተሳሰረች፣ በኢኮኖሚ ንቁ እና ሰውን ማዕከል ያደረገች ከተማ የማድረግ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ላይ መሰረት የተጣለበት የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።