በጋምቤላ ክልል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሂደት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሂደት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል
ጋምቤላ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከአጋር አካላት ጋር በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
በጋምቤላ ክልል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስቀረት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን የሚገመግም መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አርያት ኡጁሉ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በማስቀረት የሴቶችን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል።
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ያለእድሜ ጋብቻ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶች ላይ የሚያደርሱት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ከጎጂ ልማድ ጋር ተያይዞ ሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ችግር በማስቀረት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ለውጦች መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ሴቶችን በእርሻ ልማት፣ በእርባታና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ስራዎች በማሰማራት በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ረገድ አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የተገኙትን ለውጦች ይበልጥ ለማጠናከር አሁንም የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በቢሮው ግንዛቤ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ግሩም ገብረኢየሱስ እንዳሉት፤ በክልሉ በሁሉም ቀበሌዎች የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ኮሚቴ በማቋቋም ያለእድሜ ጋብቻን ጨምሮ ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት በትኩረት እየተሰራ ነው።
ቢሮው ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
መድረኩ ላይ የክልሉ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፣ በተከናወኑት ስራዎች ዙሪያ ሪፖርቶች ቀርበው ተገምግመዋል።
በውይይት መድረኩ መጨረሻ አቅም ለሌላቸው ሴቶች የእርባታ ፍየሎችና የገንዘብ ድጋፍ ለተወካዮቻቸው ተበርክቷል።