በሮም እና ሞስኮ የደመቁት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች - ኢዜአ አማርኛ
በሮም እና ሞስኮ የደመቁት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሮምና በሞስኮ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ድል አስመዝግበዋል።
የዘንድሮው የዝናሜንስኪ ሜሞሪያል አትሌቲክስ ውድድር የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደማቅ ድል የተመዘገበበት መድረክ ሆኗል።
በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደውና በዓለም አትሌቲክስ የ“F” ደረጃ በተሰጠው የ2026 የዝናሜንስኪ ወንድማማቾች መታሰቢያ የአትሌቲክስ ውድድር ላይ፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች አስደናቂ ብቃት በማሳየት ውድድሩን በድል አጠናቀዋል።
በሩሲያ ዋና ከተማ በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፥ በአራት የተለያዩ የርቀት ዓይነቶችም የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ ችለዋል።
በሴቶች የ1500 ሜትር ውድድር አትሌት ብርቄ ኃይሎም ርቀቱን በ3:58.59 በሆነ ፈጣን ሰዓት በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥታለች።
አትሌት ሳሮን በርሄ በ4:01.96 ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
በዚሁ ውድድር ላይ አትሌት ደስታ ታደለ 5ኛ፣ አትሌት ሲፈን ዳገታ 8ኛ፣ አትሌት በሻቱ ጌታ 9ኛ፣ እንዲሁም አትሌት ቤተልሔም ሙላት 15ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በሴቶች የ10000 ሜትር ውድድር አትሌት ፈንታዬ ጫኔ በ32:23.54 አንደኛ በመሆን ስታሸንፍ፣ አትሌት ቤተልሔም ኦላና በ32:25.57 ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።
ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሰላማዊት ሻምበል 4ኛ እንዲሁም አትሌት ትርንጎ ታደለ 6ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ፈጽመዋል።
በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር፣ ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የሩጫ መድረክ አትሌት ብርቱካን ገዳሙ ርቀቱን በ9:36.20 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በሴቶች 800 ሜትር ውድድር አትሌት ሀብታም ገበየሁ በ2:02.53 በሆነ ሰዓት 6ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በወንዶች የ10,000 ሜትር ውድድር ላይ አትሌት እዮብ ስመኝ እጅግ ግሩም ውጤት አስመዝግቧል።
አትሌት እዮብ ርቀቱን በ27:55.75 በማጠናቀቅ ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቋል።
በዚሁ ውድድር ላይ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሽመልስ ንጉሴ በ28:16.57 ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችሏል።
በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር አትሌት ዲንቃ ፍቃዱ ርቀቱን በ8:35.32 አንደኛ በመሆን በበላይነት አሸንፏል።
አትሌት ሂርኮ ኃይሉ በበኩሉ ርቀቱን በ8:38.24 በማጠናቀቅ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።
የ2026 ዳይመንድ ሊግ አራተኛ መዳረሻ በሆነው የሮሙ የሴቶች 5000 ሜትር ውድድር፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ በሙሉ በመቆጣጠር በበላይነት አጠናቀዋል።
በውድድሩም አትሌት ልቅና አምባው በ14:18.41 የወቅቱን የዓለም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ የባለድልነት ዘውዱን ደፍታለች።
አትሌት ልቅና አምባው የግሏን ምርጥ ሰዓት ከዓምስት ሰከንድ በላይ ማሻሻል የቻለች ሲሆን፥ የወቅቱ የርቀቱ ፈጣን በሆነው 14:18.41 ሰዓት ውድድሩን አሸንፋለች።
ይህች አትሌት ቀደም ሲል በሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።
በዚሁ የሮም ውድድር አትሌት አለሚቱ ባወቀ በ14:18.54 ሁለተኛ እንዲሁም አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ በ14:18.94 ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።