ቀጥታ፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን በመኽር እርሻ 718 ሺህ ሄክታር መሬት ይለማል

ነቀምቴ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ወለጋ ዞን በመኽር እርሻ 718 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች እንደሚለማ  የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጄ ነገሰ እንደገለጹት፤ በመኽር እርሻ 718 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ24 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

ለዚህም ለአርሶ አደሩ አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ፣ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያለው የዝናብ ሁኔታ ለግብርና ሥራው እጅግ አመቺ በመሆኑ፣ አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት ለማግኘት በንቃት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በመኽር እርሻው ከታቀደው መሬት ውስጥ እስካሁን 272 ሺህ 402 ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን አቶ ደረጄ ገልጸዋል።

ከግብዓት አንጻርም 473 ሺህ 379 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ቀርቧል ብለዋል።

ዞኑ በበቆሎ ምርት የሚታወቅ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ እስካሁን 255 ሺህ 92 ኩንታል የምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ተደርጓል ነው ያሉት።

የምስራቅ ወለጋ ዞን የጉቶ ጊዳ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ሙላቱ በበኩላቸው፤ በወረዳው 64 ሺህ 139 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 30 ሺህ 568 ሄክታሩ መልማቱን ተናግረዋል።

በወረዳው ዘንድሮ ግብዓት በወቅቱ በመቅረቡ ምንም ዓይነት የእጥረት ስጋት እንደሌለ የጠቆሙት ኃላፊው፤ እስካሁን 47 ሺህ 166 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 5 ሺህ 124 ኩንታል ምርጥ ዘር መሰራጨቱን አስረድተዋል።

የጉቶ ጊዳ ወረዳ አርሶ አደር አብዲሳ ቀናቴ፤ ማሳቸውን በክላስተር በማረስ በበቆሎ ዘር ለመሸፈን እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ዘንድሮ የተሻለ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር አቶ ተስፋ ይማም በበኩላቸው፤ በመኽር ወቅቱ 14 ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል ለመሸፈን እያረሱ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ያገኘነውን የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተጋሁ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም