ቀጥታ፡

825 የምርጫ ክልሎች ጊዜያዊ ውጤት ይፋ አድርገዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እስካሁን 825 የምርጫ ክልሎች ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ገለጹ፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በጠንካራ የሕዝብ ተሳትፎ በስኬት መጠናቀቁን አስታውሰዋል።

በምርጫው ዕለት ማለዳ 12፡00 ሰዓት ላይ ተጀምሮ የነበረው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት፣ እስከ ምሽቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ ተራዝሞ መጠናቀቁ ይታወቃል።

ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ጊዜያዊ ውጤቶች በየምርጫ ጣቢያዎቹ ሲለጠፉ መቆየታቸውን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ የየጣቢያዎቹ ውጤቶች ምስጢራዊነታቸው በተጠበቀ መልኩ ወደ የምርጫ ክልሎቹ እንዲደርሱ መደረጉንና የማዳመር ሥራው ሲከናወን መቆየቱን አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት ቦርዱ ምርጫ ባካሄደባቸው አጠቃላይ 1 ሺህ 138 የምርጫ ክልሎች መካከል፣ 825ቱ የማዳመር ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ አጠናቀው ጊዜያዊ ውጤቱን ይፋ አድርገዋል ብለዋል።

የማዳመር ስራን በመስራት ላይ ያሉ ቀሪ የምርጫ ክልሎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

እነዚህ ቀሪ የምርጫ ክልሎች ሂደቱን በጥቂት ቀናት ውስጥ አጠናቀው ውጤት ይፋ እንደሚያደርጉ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም