የሚሊሻ ሃይሉ በልማትና የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ረገድ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሚሊሻ ሃይሉ በልማትና የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ረገድ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈ ነው
ባህር ዳር፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የሚሊሻ ሃይሉ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በልማትና የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ተግባር ላይ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን የምስረታ በዓል አከባበርና የእውቅና ፕሮግራም "የ30 ዓመታት የጀግንነት ታሪክ፤ ለዘላቂ ሰላም፣ ለሀገር ኩራት!" በሚል መሪ ሀሳብ በባህር ዳር ከተማ እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ በበዓሉ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ የሚሊሻ ሀይሉ ላለፉት 30 ዓመታት የህዝብና መንግስት አደራን በመወጣት አኩሪ ታሪክ ሰርቷል።
ተግባሩን በማስቀጠልም የጠላቶችን ሴራ ለማክሸፍ ከፌደራልና ከክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀትም ሰላምን በማስፈንና በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ግንባር ቀደም ተግባር ማከናወኑን አንስተዋል።
የሚሊሻ ሃይሉ የ30 ዓመታት ጉዞ በዓል ሲከበርም ለአገር፣ ለክልሉና ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በመዘከር መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዋል።
የክልሉ ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ በበኩላቸው የክልሉ ሚሊሻ ኃይል ህዝባዊነትን በመላበስ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ታሪክ የማይረሳው ጀግንነት ሲፈጽም መኖሩን ገልጸዋል።
በሰላም ጊዜ አርሶ አደር፣ በችግር ጊዜ ደግሞ ወታደር በመሆን የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር አስጠብቆ ለማቆየት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ተቋሙ በከፍተኛ ደረጃ ሪፎርም እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ይህም ጠንካራ ተቋም በመገንባት ለሚሊሻ አባላት ተልዕኮን በላቀ ብቃት ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉን ስናክብርም ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲሉ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግና የሚሊሻ አባላት ቤተሰቦች የሚደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍና እንክብካቤ አጠናክሮ ማስቀጠል ላይ በማተኮር ነው ብለዋል።
በእለቱም በተቋሙ የላቀ አፈጻጸም ላሳዩና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ መስዋዕትነት ለከፈሉ አባላትና ቤተሰቦቻቸው እውቅና የመስጠት መርሃ ግብር መካሄዱም ተመልክቷል።