ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው
ሰመራ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናት እና ምርምር ተግባራት ማገዝ እንዳለባቸው የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዘካሪያስ ኤርኮላ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል የህግና ፍትህ ኢንስቲቲዩት ጋር በመተባበር "ህገ-ወጥ ፍልሰት እና የሰዎች ዝውውር፤ የህግ፣ ማህበራዊ እና ተቋማዊ አመለካከቶች" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው አገር አቀፍ ሲምፖዚየም በሰመራ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ዘካሪያስ ኤርኮላ (ዶ/ር)፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰትን ለመከላከል የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በጥናትና ምርምር ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
የዚሁ አካል በሆነው በዚህ ሲምፖዚየም ላይ የቀረቡት የምርምር ፅሁፎች፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የወጡ ህጎች አፈፃፀምና አተገባበር ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በውይይቱ የሚገኙት ግኝቶች ለፖሊሲ አውጪዎችና ለህግ ማሻሻያ ስራዎች በግብአትነት እንደሚያገለግሉም ገልጸዋል።
ኢንስቲቲዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በህጎች አተገባበር ላይ የግንዛቤና የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፤ ይህም ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድና የፖሊሲ ግብአቶችን ለማፍለቅ ትልቅ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱረህማን ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ህገ-ወጥ ፍልሰትና የሰዎችን ዝውውር ለመግታት የድርሻውን እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የአፋር ክልል ወደ የመንና ጅቡቲ ለሚደረገው ህገ-ወጥ ስደት እንደ መስመር የሚያገለግል በመሆኑ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ተቋማቸው በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም ስኬታማነት ዩኒቨርሲቲው ለህብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ለባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት እና ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማካሄድ ረገድ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አክለዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የህግና ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ዲኖች፣ ተመራማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።